ቀጥታ፡

በመዲናዋ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችና ሌሎች የደንብ መተላለፎችን አስቀድሞ ለመከላከል ከሰላም ሰራዊትና ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በመዲናዋ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችና ሌሎች የደንብ መተላለፎችን አስቀድሞ ለመከላከል ከሰላም ሰራዊትና ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

ቢሮው ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትና ከሰላም ሰራዊት ተወካዮች ጋር በመዲናዋ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ምክክር አድርጓል።  
 

የቢሮው የጸጥታ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ጌታሁን አበራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  በመዲናዋ የተለያዩ ወንጀሎችና ደንብ መተላለፎችን ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው።  

የጸጥታ መዋቅሩ ከሰላም ሰራዊቱና ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ ሰላምን በማረጋገጥ እንዲሁም ወንጀሎችን በመከላከል አዎንታዊ ውጤት ማስመዘገብ መቻሉን ገልጸዋል።  

የሰላም ሰራዊት አባላቱ በተለይም የወንጀል መንስኤዎችን የመለየትና ለፖሊስ ጥቆማ በማድረጋቸው ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት እንዲቀለበሱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ያም ሆኖ አሁንም ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም ንጥቂያና ሥርቆት የመሰሉ የወንጀል ድርጊቶች በመዲናዋ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።  

በሌላ በኩል ጫት ማስቃም፣ ሺሻ ማስጨስና ሌሎች መዲናዋን የሚያውኩ ደንብ መተላለፎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። 

በመሆኑም ቢሮው ከሰላም ሰራዊትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከልና የከተማዋን ጸጥታ ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከጸጥታ አካሉ በሚሰጣቸው ስምሪት መሰረት የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ፖሊስም የ'ሰላም ሰራዊት' ለጸጥታ ሥራው አጋዥ ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ ተገቢውን እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ833 ብሎኮች 188 ሺህ 773 የሰላም ሰራዊት አባላት ስራ ላይ ይገኛሉ። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም