ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 114 የተራቆቱ ተራሮችን ለማልማት እቅድ መያዙ ተገለጸ  

ዲላ ሰኔ 10/2015 (ኢዜአ):- በደቡብ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 114 የተራቆቱ ተራሮችን ለማልማት መታቀዱን የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ዛሬ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ሽጋዶ ቀበሌ ተጀምሯል።
 

የደቡብ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንዳሉት በክልሉ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎችን ገጽታ በመቀየር የግብርና ምርታማነትን ከማሻሻል ባለፈ 12 በመቶ ብቻ የነበረውን የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 16 ነጥብ 7 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።

ከመጀመሪያው ምዕራፍ ተሞክሮ በመቀመርና በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዘንድሮው መርሐ-ግብር በደቡብ ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮና የችግኝ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰው ከሚተከሉ ችግኞች 50 በመቶ የሚሆነው ፍራፍሬ፣ ቡና እና አገር በቀል ዛፎች መሆናቸውንም ነው አቶ ዳንኤል ያስረዱት።

የችግኝ ተከላ ጥራት በማሻሻል በቀጣይ ሶስት አመታት ከ342 የተራቆቱ ተራሮችን ለማልማት መታቀዱን ጠቅሰው ዘንድሮ 114 ለማልማት ልየታ መደረጉን አመልክተዋል።
 

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር የደን ሽፋናችን ከማሳደግ ባለፈ ከድህነትን ለመላቀቅ የምናደርገው ጥረት ግብ እንዲመታ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በተያዘውም ዓመት ጥራቱን በጠበቀ የችግኝ መርሐ-ግብር በፍራፍሬ እና አገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም የደን ሽፋንና የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የስራ አጥነት ችግር ለመቀረፍ ታሳቢ ተደርጎ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
​​​​​​​

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ''የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን አደጋ ለመቋቋም በተለይ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ዛሬ ዛፍ መትከል አለብን'' ብለዋል።

በተለይ ዛፍ በመትከል የነገ ምግባችንን ዛሬ ከማዘጋጀት ባለፈ ምቹ አገር ለነገ ትውልድ ለማስረከብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

''የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል እያለን ልንራብ አይገባም'' ያሉት ከንቲባዋ ''ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና በጋራ መስራት አለብን'' ብለዋል።
 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት  አፈ- ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር፣  "አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አገርን ከድህነት ለማላቀቅ የሚደረግ የአርበኝነት ዘመቻ ነው" ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ስኬታማነት ሊረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአረንጓዴ አሻራ ስራን የበለጠ ለማስፋፋት ለሰርቶ ማሳያ የሚሆን አንድ ሄክታር መሬት ተረክበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም