የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ እየተሰራ ነው- የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ እየተሰራ ነው- የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሕብረት
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015 (ኢዜአ) ፦ የዩኒቨርሲቲ ዕጩ ምሩቃን መውጫ ፈተና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት ለተግባራዊነቱ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሕብረት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ያቦነሽ ለኢዜአ እንደገለጸው የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መውጫ ፈተና ሪፎርሞች የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አላቸው።
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የትምህርት ስርዓቱን ወደ ተግባር ተኮር በማሸጋገር የተሻለ የሰው ሀብት ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁሟል።
በዚህም ሕብረቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለመውጫ ፈተናው መሟላት ያለባቸው ቁሳቁሶች እንዲሟሉና አሰራሮች እንዲስተካከሉ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል።
የመውጫ ፈተና በመርህ ደረጃ አሳማኝ ቢሆንም የፈተናው አሰጣጥ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፈተናው እንዴትና በምን መልኩ ይሰጥ በሚለው ዙሪያ ተማሪዎች ጥያቄዎች እንዳሏቸው ጠቁሟል።
ሕብረቱም እንደ ተወካይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተማሪዎች ጥያቄ መፍትሄ እንዲያገኝ እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጾ፤ ተማሪዎችም ራሳቸውን እያዘጋጁ በትዕግስት መጠበቅ አለባችው ብሏል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ አስተዳደር ጉዳይ ዴስክ ኅላፊ አቶ አብዱ ናስር፤ መውጫ ፈተናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ፈተናው ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብና በተግባር ተኮር ትምህርቶች ብቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ በፈተና አሰጣጥ ሁሉን አቀፍ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህ ሰዓትም ፈተናው እና የፈተና አሰጣጥ ፕሮግራም ለዩኒቨርሲቲዎች መላኩን ገልጸው፤ ተማሪዎች ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል የትምህርት ማካካሻዎች ሲከናወኑ መቆየታችውን ነው ያነሱት።
የመውጫ ፈተናው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የራሱ ተግዳሮቶች ሊኖሩበት ቢችልም የፈተና አሰጣጡ ስኬታማነት ከወትሮው በተለየ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በሂደት የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት ከተማሪ አደረጃጀቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ተማሪዎችም ከወዲሁ ራሳቸውን አዘጋጅተው ለፈተና እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።