ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015 (ኢዜአ)፦ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለአገራዊ ፕሮጀክቶች እና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ጥሪ አቀረቡ።

ዶክተር መሐመድ በኬንያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውይይት አድርገዋል።

በመንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች፣ የአገራዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና በኤምባሲው የሚሰጡ አገልግሎቶች ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን አምባሳደር ወርቃለማሁ ደስታ ውይይቱ መንግስት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ዳያስፖራው ለአገራዊ ፕሮጀክቶች እና ወቅታዊ ጥሪዎች እየሰጠ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ለአገራዊ ችግሮች የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዳያስፖራ አደረጃጀት አባላትና ተወካዮች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ተወካዮቹም ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል እና ከኤምባሲው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ቃል መግባታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም