ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለማከናወን እየተሰራ ነው -  የክልሉ ሲቪል ምዝገባ ኤጀንሲ 

ጭሮ ሰኔ 10/2015(ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ሲቪል ምዝገባ ኤጀንሲ ገለጸ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የወሳኝ ኩነት አሰራር አስመልክቶ በዞኑ ለሚገኙ 80 ለሚሆኑ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ሲቪል ምዝገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቤኛ ተረፈ፣ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አኳያ የምዝገባ አሰራሩን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉን የወሳኝ ኩነት መረጃ አያያዝ በብቁ ባለሙያዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማከናወን ለሕዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የሚተገበረውን የ'ብሔራዊ መታወቂያ' እቅድ ለማሳካት ከወዲሁ የባለሙያዎችን አቅምና ክህሎት መገንባት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተማም ሀምዳ በበኩላቸው በዞኑ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሰራርን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ከግብረ ሰናይ ድርጅት በተገኘ 11 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎች መገዛታቸውን አስረድተዋል።

የንድፈ ሀሳብ ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከስልጠናው በኋላ ለአንድ ወር የሚቆይ የተግባር ስራ ልምምድ እንደሚኖር ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም