ቀጥታ፡

ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራመርሃ ግብር 3 ሚሊዮን አገር በቀል ችግኞች ተዘጋጅተዋል- የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢኒስቲትዩት

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015(ኢዜአ)፡-ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 3 ሚሊዮን አገር በቀል ችግኞች ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተተገበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች  መተከላቸው  ይታወቃል፡፡

ዘንድሮ በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጥምር ደንና ለአገር በቀል ዕጽዋቶች ልዩ ትኩረት መሰጠቱም እንዲሁ፡፡ 

በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት የደንና የግጦሽ መሬት ብዝሃ ሕይወት ዳይሬክተር አበራ ስዩም እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ሥራ ላይ ቅድሚያ ይሰጥ  የነበረው ከውጭ ለመጡ ዕፅዋት እንደነበር ተናግረዋል።

ይሁንና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ለአገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢኒስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  ከተጀመረ ጀምሮ  5 ሚሊየን አገር በቀል ችግኞችን  ማሰራጨቱን የገለጹት ሀላፊው፤ ለዘንድሮው ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው  3 ሚሊዮን  ችግኞች መዘጋጀታቸውን  ገልጸዋል።
 

ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል እንደ ዝግባ፣ ዋርካ፣ ጥቁር እንጨትና መሰል የደን ተክሎችን ጨምሮ ለባህላዊ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዕፅዋቶች ይጠቀሳሉ ብለዋል። 

የተዘጋጁት ችግኞች በኢኒስቲትዩቱ ስር ባሉት 9 ማዕከላት ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ ለተከላውም ባለድርሻ አካላትንና  የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፈ  የቦታ ዝግጅት እየተከናወነ  መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

አገር በቀል ዕፅዋትን መትከል የአካባቢ ሥነ -ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ያሉ ዕፅዋቶች መልሰው እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛን እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ፤የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝሃ-ህይወት ጥበቃ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማጠናከር ተቋሙ  እየተመናመኑና  በመጥፋት ላይ ያሉ ዕጽዋትን በመንከባከብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አገር በቀል ችግኞችን መትከል  የአፈር ለምነትን በመጨመር የብዝሃ ህይወትን መመናመን ለማስቀረት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት። 

ኢኒስቲትዩቱ አሁን ላይ በተለይም ለመጥፋት የተቃረቡ ዕጽዋቶችን በአገር በቀል ለመተካት ችግኞችን በስፋት  የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በአገር አቀፍ ደረጃ ከተተከሉት ችግኞች መካከል  52 በመቶ የሚሆኑት የጥምር ደን እርሻ ሲሆኑ ቀሪው የደን ችግኞች ናቸው፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም