በትግራይ ክልል ሁለት ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም ለማልማት እየሰሩ ነው - የክልሉ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ሁለት ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም ለማልማት እየሰሩ ነው - የክልሉ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል
አክሱም ሰኔ 10/2015(ኢዜአ):- በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም የማልማት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ የክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል አስታወቀ።
በማዕከሉ የጤፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ኃይሉ ለኢዜአ አንደገለጹት በሁለቱም ዞኖች 50 ሺህ አርሶ አደሮችን ወደ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ለማሸጋገር በ850 የጤፍ ክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
አርሶ አደሮቹ ጤፍን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴ 12 ሺህ 750 ሄክታር ማሳ በጤፍ ምርጥ ዘር እየሸፈኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ አርሶ አደሮቹ ማሳቸውን በእርሻ ትራክተር ማረስ መቻላቸው በበሬ ለማረስ እና አረም ለማረም የማያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ለሌሎች የልማት ስራዎች እንዲያወሉ ያስችላቸዋል።
በኩታ ገጠም ተደራጅተው እርሻቸው አዘምነው መስራት መጀመራቸው ምርታማነትን አሳድገው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ምርት ለገበያ አቅርበው ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል።
አርሶ አደሮቹ ግብርናን በዘመናዊ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቲዩት የበጀት ድጋፍ እንዳደረገላቸውም ነው አቶ ቴዎድሮስ የገለጹት።
በማዕከሉ በኩል በስድስት ወረዳዎች ለሚገኙ የአቅም ውስንነት ላለባቸው ሴት አርሶ አደሮች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በትራክተር የማረስ ስራ እየተከናወነ እና ማዕከሉ የጤፍ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ከሁለገብ የሕብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀፀቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስዩም ዓለማየሁ በበኩላቸው ግብርናን በእርሻ ትራክተር ማረስ በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ጉልበትና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀርላቸው ገልጸዋል።
አርሶ አደር ብርሃኑ ታከለ የእርሻ ትራክተር ተጠቅመው ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን መተግበር የአፈር ለምነት ጠብቆ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን እና አረምን ይቀንሳል ብለዋል።