ቀጥታ፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ

ሚዛን አማን ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል፡፡

በመተባበር መንፈስ አቅመ ደካሞችን በተቻለ አቅም ካለው አካፍሎ በመርዳት ሰብዓዊ ግዴታን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተጀመረው  የቤትና ሌሎች በበጎ ፈቃድ የሚሰሩ የድጋፍ ሥራዎች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ መረባረብ እንደሚገባ አክለዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በክልሉ ችግኝ የተከሉ ሲሆን የክልሉ ህዝብ ለተፈጥሮ የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

"የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለእኛ ሞራል የሆነ የኢትዮጵያ ነጸብራቅ ነው" ብለዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ አወል አክለውም የክልሉ ህዝብ ከደን ጋር ተቆራኝቶ የመኖር ሚስጥር ለዓለም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያሉ እምቅ አቅሞችን ለሀገራዊ ብልጽግና ለመጠቀም አመራሩ ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት አኳኃን በትበብር እና በአንድነት መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው ብልጽግና አዳዲስ ትልሞችን እያመነጨ የሚተገብር ፓርቲ ነው ብለዋል።

ከትልሞች ውስጥ አንዱ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር መሆኑን በመጥቀስ።

በተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ተግባራት ከፓርቲው ትሩፋት መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላና የበጎ-አድራጎት ተግባር የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በቦንጋ ከተማ እየተሰጠ ካለው የአመራር ስልጠና ጎን ለጎን የተካሄደ ሲሆን የፓርቲውን ሥልጠና ውጤታማ ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ የሁልጊዜ ተግባር የሆኑ ጉዳዮችን አያይዞ መተግበር መቻሉ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የተጀመረው የአቅመ ደካማና የአረጋውያን ቤት የማደስ ሥራ አቅም ያላቸውን ሰዎች በማስተባበር የሚፈጸም መሆኑን አስታውቀዋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘውን የሚዛን አማን አየር ማረፊያን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም