በመዲናዋ ተግባራዊ የተደረገው የቤት ግብር ማሻሻያ የዜጎችን አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊተገበር ይገባል - ግብር ከፋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ተግባራዊ የተደረገው የቤት ግብር ማሻሻያ የዜጎችን አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊተገበር ይገባል - ግብር ከፋዮች
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ተግባራዊ የተደረገው የቤት ግብር ማሻሻያ የዜጎችን አቅም ታሳቢ ያላደረገ እና በቂ ግንዛቤ ያልተፈጠረበት ነው ሲሉ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ "ማሻሻያው ወቅቱን የዋጀና ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የተከናወነ ነው" ሲል ገልጿል።
በአዲስ አበባ በ1968 ዓ.ም የወጣው የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ በየጊዜው እንደሚሻሻልና ወቅታዊ እንደሚደረግ የሚደነግግ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።
የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማስፋትና እያደገ የመጣውን የነዋሪዎች ፍላጎት ለማሟላት የገቢ ምንጮችን ማስፋትና የክፍያ ተመንን ወቅታዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በጥናት መለየቱን ገልጿል።
በዚህም አዲስ የቤት ግብር ማሻሻያ በግለሰብና በጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በሕንጻዎች፣ በሊዝ ይዞታ እና በተቋማት ላይ የተጣለ ሲሆን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየካ ከፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና ስድስት እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና አምስት ግብር መክፈያ ጣቢያ ቅኝት አድርጓል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ግብር ከፋዮች እንደሚሉት ፤ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ቢሆንም የተጠየቀው ግብር የዜጎችን አቅም ያገናዘበ አይደለም ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው ግብር ምን ያህል ፍትሐዊ ነው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አንስተው ግብሩ ከመጣሉ በፊት በቂ ግንዛቤ ተሰጥቶ ወደ ስራ መግባት ነበረበት ሲሉ ገልጸዋል።
የሚከፈለው ግብርና ልኬቱ የተናበበ እና አሰራሩን ግልጽ የማድረግ ጉዳይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የግብር ክፍያ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የቅንጅት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘገየ በላይነህ ፤ "ነዋሪዎች ከዚህ በፊት ይከፍሉት የነበረው ግብር በጣም ዝቅተኛ ነበር" ብለዋል።
ለአብነትም በመዲናዋ ከሚገኙ የቤት ግብር ከፋዮች መካከል ከ 20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከ10 ብር ያነሰ ግብር እንደሚከፍሉ ጠቁመው ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆት ደግሞ ከ1 ብር ያነሰ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ግብሩ አሁን ካለው አገልግሎት ጋር የሚጣጣም መሆን ይገባዋል ያሉት አቶ ዘገየ አሁን ተግባራዊ የተደረገው የቤት ግብር ማሻሻያ ይህንን ከግምት ያስገባና በጥናት የተረጋገጠ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት የዜጎችን ጫና ለመቀነስ በማሰብ የዚህን ዓመት ግብር ግለሰቦች 50 በመቶ እና ድርጅቶች 75 በመቶ ብቻ እንዲከፍሉ በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የተሻሻለው የቤት ግብር ተግባራዊ የተደረገውም የዚህን ዓመት ግብር እስከ የካቲት 30 ቀን 2015 ያልከፈሉ ነዋሪዎች ላይ ብቻ መሆኑንና የዚህን ዓመት ግብር በጊዜ ገደቡ መሰረት እስከ የካቲት 30 ድረስ የከፈሉ ነዋሪዎች በቀድሞ የዋጋ ተመን መሰረት መክፈላቸውን አስረድተዋል።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ግብሩ እየተጣለ ያለው የቤቱ ዓይነት፣ የቤት ስፋት፣ የቦታ ደረጃ እና የቤቱን አገልግሎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው።
ይሁን እንጂ በግብር አጣጣልና አሰባሰብ ሂደት ቅሬታ ያለው ዜጋ ቅሬታው በየደረጃው የሚታይበት ስርዓት መዘርጋቱን አመልክተዋል።