በአፍሪካ በግጭቶች ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ለመደገፍ ያጋራ ጥረት ያስፈልጋል- የአፍሪካ ተማሪዎች ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ በግጭቶች ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ለመደገፍ ያጋራ ጥረት ያስፈልጋል- የአፍሪካ ተማሪዎች ሕብረት
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ በግጭቶች ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ የጋራ ጥረት እንደሚሻ የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ሕብረት አስታወቀ።
የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።
የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት ኦሲሲኮ ኦስጎኒ በቀኑ አከባበር ላይ እንዳለው ግጭት፣ የገንዘብ እጦት እና የትምህርት ተደራሽነት ለአፍሪካውያን ተማሪዎች ትልቅ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል።
በተለይም በአፍሪካ በሚከሰቱ መልከ ብዙ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ብሏል።
በዚህም ሀገራት ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሄ በመፈለግ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስና የትምህርት ዘርፉን ማገዝ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በሰላም መቋጨቱ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለነበሩ ተማሪዎች ትልቅ እፎይታን መሆኑን ገልፀው፤ ሌሎች ሀገራትም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ተማሪዎችን መታደግ አለባቸው ነው ያለው።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ያቦነሽ በበኩሉ በአፍሪካ የመማር ማስተማር እና የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብሏል።
ሕብረቱም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከር በትምህርት ተደራሽነትና የዜጎችን መብቶች ማስጠበቅ ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው፤ አፍሪካን የተሻለች አህጉር ለማድረግ በትምህርት፣ በጤናና፣ በክህሎት ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።
ለዚህም የትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ቅንጅታዊ ስራዎችን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ አስተዳደር ኅላፊ አቶ አብዱ ናስር ኢትዮጵያ ከዘላቂ ልማት ግቦች አንዱ በሆነው በትምህርት ዘርፍ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።
በዘርፉ መልከ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ገልጸው ኢትዮጵያ በተለይም በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ አተኩራ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
በከብረ በዓሉ ላይ የመላው አፍሪካ ተማሪዎች ሕብረት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ተማሪዎች ቀን የሚከበረው በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጣር ሰኔ 16 ቀን 1976 በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በግፍ ለተጨፈጨፉ ጥቁር አፍሪካውያን ተማሪዎች መታሰቢያነት ነው።