ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባኤ በኢትዮጵያ ያካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባኤ በኢትዮጵያ ያካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ):-ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) በአፍሪካ ላይ ያተኮረውን ጉባኤውን ሰኔ 13 እና 14 2015 በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
“የአቪዬሽን ዘርፉን አቅም መጠቀም” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ጉባኤ በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ያሉ እድሎች እና ፈተናዎች ላይ እንደሚመክር ገልጿል።
በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ደህንነት በማሻሻል፣አዋጪ የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፣የአየር ትስስርን በማጠናከር፣የዘመነ የአየር መንገዶች የገበያ አገልግሎት አሰጣጥ፣መሰረተ ልማት እና አቅም ግንባታ፣የሰለጠነ ሰው ኃይል ማፍራት እና ሌሎች በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በጉባኤው ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ አየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣የአቪዬሽን ዘርፍ መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች፣የአውሮፕላን አምራቾች፣ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የአየር መንገድ ማህበራት፣የዘርፉ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል።
ዋና መቀመጫውን በካናዳ ሞንትሪያል ያደረገው ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር(አያታ) የተቋቋመው እ.አ.አ በ1945 ነው።
ማህበሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ123 አገራት የተወጣጡ 303 አየር መንገዶችን በአባልነት አቅፏል።
አያታ ዓለም የሚያስተሳሰር እና የሚያበልጽግ ትርፋማና ደህንነቱ የተጠበቀ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ለመፍጠር የሚሰራ ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋም ነው።