በስደተኞች ጉዳይ ላይ ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ተቋም(ኢኤሲ) የሚኒስትሮች ጉባኤ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በስደተኞች ጉዳይ ላይ ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ተቋም(ኢኤሲ) የሚኒስትሮች ጉባኤ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ):- የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ተቋም(ኢኤሲ) በስደተኞች ጉዳይ በዩጋንዳ ካምፓላ ሲያካሂዱት የነበረው የሚኒስትሮች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባኤ ላይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
ጉባኤው በባለሙያዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ የቀረቡለትን አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
በሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም የተመራ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በጉባኤው ላይ ተሳትፏል።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት በቀጣናው የስደተኞች ጉዳይን አስመልክቶ እያከናወኑ የሚገኘውን ስራ ለጉባኤው አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለስደተኞች ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያመጡ የተለያዩ ፖሊሲዎች እና መርሐ-ግብሮችን ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ጫና እና ኃላፊነት በመጋራት መንፈስ” የሰብአዊ እና የልማት እርዳታን ሊያመጣጥን ይገባል ብለዋል።
የመፈናቀል መንስኤ ለሆኑ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በጉባኤው ላይ በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተወካዮች ተሳትፈዋል።