ጃፓን በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች-አምባሳደር ኢቶ ታካኮ - ኢዜአ አማርኛ
ጃፓን በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች-አምባሳደር ኢቶ ታካኮ
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ) ጃፓን በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ፡፡
ጃፓን በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታና ሳኒቴሽን ፕሮግራም የሚውል 8 ነጥብ1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፖ ጋር ተፈራርመዋል።
ድጋፉ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ ግጭት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ያለመ ነው ተብሏል።
መሰረታዊ የሆኑ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ትምህርት ቤቶችን ያሉ መሰረተ ልማቶችን እና የሳኒቴሽን እና ሃይጂን ፕሮግራምን ለመደገፍ ድጋፉ እገዛ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በድጋፍ ስምምነቱ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ድጋፉ በጦርነቱ ለተጎዱ የአማራና የትግራይ አካባቢዎች ለትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታና ሳኒቴሽን ፕሮግራም የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ የንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦትን ለማሻሻል ይረዳል ብለዋል።
ጃፓን በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው የጠቆሙት፡፡
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው፤ ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ይውላል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹን መልሶ በመገንባት 12ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀው በሳኒቴሽን እና በሃይጂን ፕሮግራም ደግሞ 47 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።
በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት በትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ መዝገቡ ቢያዝልኝ ናቸው።
ድጋፍ 17 ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ድጋፉ በኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እንደሚረዳም ተጠቁሟል።