ቀጥታ፡

የዳያስፖራ ምሁራን በአገር ቤት ተቋማት በጊዜያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የሙከራ ፕሮጀክት ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እና የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት(አይ ኦ ኤም) የዳያስፖራ ምሁራን በአገር ቤት ተቋማት በጊዜያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የሙከራ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የተፈረመው በኬንያ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት(አይ ኦ ኤም) ጽህፈት ቤት እና የየአገራቱ የዳያስፖራ ቢሮዎች በነበራቸው የሁለት ቀናት መድረክ ላይ መሆኑ ተገልጿል።


 

የሙከራ ፕሮጀክቱ ውጤታማነት ተፈትሾ በቀጣይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተሞክሮውን ለማስፋት እንደሚሰራም በመድረኩ ላይ መገለጹን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት(አይ ኦ ኤም) የዳያስፖራ ምሁራን በአገር ቤት ተቋማት በጊዜያዊነት አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራን ከተለያዩ አገራት ጋር የመስራት ተሞክሮ እንዳለው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከጅማ፣ ሃዋሳ፣ ወሎ እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የዳያስፖራ እውቀትና ክህሎት ሽግግር የሚመራበት ስትራቴጂ ማስጠናቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

የሙከራ ፕሮጀክቱ ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚረዳም ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም