ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ያለውን ልማዳዊ የልኬት ተግባር በዓለም አቀፍ የአለካክ ደረጃዎች ለመቀየር እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ያለውን ልማዳዊ የልኬት ተግባር በዓለም አቀፍ የአለካክ ደረጃዎች መቀየር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የልኬት መሳሪያዎችን ጥራት በማስጠበቅ ሳይንሳዊ ልኬት ለማከናወን የተመሰረተ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ የዓለም አቀፍ ሚዛንና መሥፈሪያ ቢሮ ተባባሪ አባል ሲሆን ዓለም የደረሰበትን የሳይንስ መሳሪያዎች በመጠቀም ግብርናን ማዘመንና የኢንዱስትሪ ምርትን ማሳደግ የሚያስችሉ የልኬት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱ አባጊቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የተጠበቀ ልኬት በመጠቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ የሥነ-ልክ ተቋማት መካከል አንዱ የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው፡፡

ለዚህም ከጀርመን፣ ከኮሪያ፣ ከቱርክና ከግብፅ የሥነ-ልክ ተቋማት በልኬትና ሳይንሳዊ መሣሪያዎችን በተመለከተ ልምዶችን በመቅሰም እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ባሰለጠናቸው ባለሙያዎች አቅሙን እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት በኬሚካል ልኬት መሣሪያዎች የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ እና የምግብ ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በመለካት ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እናደረጋለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎችን ለመፈተሽና የሳይንስ መሳሪያዎችን ለመጠገን የመንግስት አቅም ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለኃብቶች በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በላቦራቶሪና የሳይንስ መሳሪያዎች ጥገና ወርክሾፕ ለሚያቋቁሙ ባለሀብቶች አስፈላጊውን የቴክኒክና የማማከር ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በካሊብሬሽን ፍተሻ መጠነኛ ጉደለት ኖሮባቸው አገልግሎት የማይሰጡ የሳይንስ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ኢንስቲትዩቱ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል ብለዋል፡፡

ዘርፉን የሚቀላቀሉ ተዋንያን የግብር እፎይታና የመሥሪያ ቦታ ማግኘት የሚችሉበት አሰራርን በማዘጋጀት ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መላኩን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ርዝመትን በክንድ፣ ስፋትን በገመድ፣ የእህል ግብይትን በጣሳና በቁና መለካት ዛሬም ድረስ በስፋት የሚስተዋል ልማዳዊ አሰራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሲሚንቶ የተሰራ ባህላዊ የክብደት መለኪያን የሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶክተር አብዱ፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የልኬት ባህል ለማዳበር ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘባቸው የሙቀት፣ መጠን፣ ሚዛን፣ ግዝፈት፣ ግፊትና ኤሌክትሪክ ልኬቶች በየዓምስት ዓመቱ እድሳት ይደረግለታል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በማዕከል ያለውን ጫና ለመቀነስ በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ በድሬዳዋና በሐዋሳ ቅርንጫፍ ከፍቶ የካሊብሬሽንና የሳይንስ መሣሪያዎች ጥገና ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም