የሶዶ-ዲንኬ 86 ነጥብ 22 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 92 በመቶ ተጠናቋል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የሶዶ-ዲንኬ 86 ነጥብ 22 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 92 በመቶ ተጠናቋል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፦ የወላይታ እና ጋሞ ዞኖችን የሚያገናኘው የሶዶ-ዲንኬ 86 ነጥብ 22 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ 92 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ቻይና ሬይልዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር በሆነ ወጪ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
እስካሁን የፕሮጀክቱ 75 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር አስፋልት የማንጠፍ ስራ መከናወኑንና ከአጠቃላይ የግንባታ ስራው 92 በመቶው መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።
ቀሪ የግንባታ ስራዎችን እስከ ታህሳስ ወር 2016 ለማጠናቀቅ እቅድ መቀመጡን አመልክቷል።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች በወቅቱ እልባት አለማግኘታቸው፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች ግብዓት እጥረት እና የዋጋ መናር በግንባታው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጿል።
ከወሰን ማስከበር ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን መቅረፍ መቻሉንና በስራ ተቋራጩ በኩል ከገንዘብ ፍሰት ጋር የተያያዙ ችግሮቹን ቀርፎ ግንባታውን እንዲያፋጥን በአስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል መደረጉን ጠቅሷል።
የመንገዱ የቀድሞ ይዞታ በጠጠር ደረጃ የነበረ እና በተለያዩ ጊዜያት የመሸርሸር አደጋ እየደረሰበት መቆየቱን የገለጸው ተቋሙ አካባቢው ካለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና አገራዊ ፋይዳ አንጻር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ፕሮጀክቱ እውን ሲሆን በዞኖች መካከል የንግድ ትስስር ማጠናከርን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሉት ነው አስተዳደሩ ያስታወቀው።
የዚሁ መንገድ ቀጣይ ምዕራፍ የዲንኬ-ሳውላ ኮንትራት ሁለት አስፋልት መንገድ በግንባታ ሒደት ላይ እያለ ከአፈጻጸም ጋር ባጋጠሙ ችግሮች ግንባታው እንዲቋረጥ መደረጉ አውስቷል።
በአሁኑ ጊዜ ግንባታውን ለማስቀጠል ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው የስራ ተቋራጮች እንዲጫረቱ መጋበዛቸውንና ሂደቱን በማጠናቀቅ በአዲሱ በጀት ዓመት ግንባታው ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስተዳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።