ቀጥታ፡

 በእንስሳት እርባታ ዘርፍ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ዲላ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

ዲላ ሰኔ 9/2015 (ኢዜአ):- ዲላ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያቋቋመው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማእከል ዛሬ አገልግሎት ጀምሯል።

ማዕከሉ በቀን ከ300 ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ መኖ የማምረት አቅም እንዳለው ተመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ማዕከሉ ዛሬ ምርት በጀመረበት ወቅት እንዳሉት አካባቢው ለግብርና ዘርፍ አመቺ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ሀብቶቹን በአግባቡ በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ "በተለይ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ያለውን አቅም በመጠቀም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው " ብለዋል።

ይሁንና የመኖ አቅርቦት ውስንነት ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በሚያከናውናቸው ተግባራትና ለአካባቢው ማህበረሰብ የእንስሳት እርባታ ላይ ጫና እያሳደረ ነው " ብለዋል ።

በእንስሳት እርባታ ጥራቱን የጠበቀ የመኖ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩን ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል ማቋቋሙን አስታውቀዋል።

ማዕከሉ ወደ ምርት መግባቱ በዘርፉ የሚስተዋለውን የመኖ አቅርቦት እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የዶሮ ጫጩት አስፈልፍሎ በማከፋፈል የአቅርቦትና ፍላጎት ትስስርን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም  አመልክተዋል።

እንዲሁም ሥራ አጥ ወጣቶችን በመኖ አቅርቦትና በእርባታ በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። 

የዩኒቨርሲቲው የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደረጀ አንዱአለም በበኩላቸው ማዕከሉ በቀን ከ300  ኩንታል በላይ የተቀነባበረ መኖ በማምረት በአካባቢው የሚስተዋለውን የመኖ አቅርቦትና የዋጋ ንረት ለማቃለል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ማዕከሉ የተቀነባበረ መኖ ከማቅረብ በላይ፤ በዘርፉ ሀገራዊ ለውጥ ሊያረጋግጡ የሚችሉ የመኖ ማቀነባበሪያ ምርምሮችን ለማከናወን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

በቀጣይ ጥራት ያለው መኖ ለማቅረብና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚሰራም ዶክተር ደረጀ አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዶሮና በእንስሳት እርባታ በስፋት በመሰማራት የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሮች እንዲደርሱ ከማድረግ ባለፈ  የእንቁላልና የሥጋ ምርት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም