በከተሞች የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተሞችን ዘላቂ ዕድገትና ውበት በጠበቀ አግባብ ሊተገበሩ ይገባል- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተሞችን ዘላቂ ዕድገትና ውበት በጠበቀ አግባብ ሊተገበሩ ይገባል- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፦ በከተሞች የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የከተሞችን ዘላቂ ዕድገትና ውበት በጠበቀ አግባብ ሊተገበሩ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አሳሰበ።
የከተሞች ውበት፣ ሳቢነት፣ ምቹነት አጠቃላይ መልክና ገጽታ የሚወሰነው ከተቆረቆሩበት ጊዜ ጀምሮ በመሪ ዕቅዳቸው መሰረት በሚደረግላችው ሁሉን አቀፍ የውበትና ጽዳት ስራዎች መሆኑ እሙን ነው።
ከተሞች ከባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መልክና ማንነታቸው ባሻገር ዕጽዋትን ጨምሮ ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙና ዘመኑን የዋጁ መሆናቸው ለነዋሪዎች ምቹ እና ለጎብኚዎችም ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
ለዚህም ፈጣን የከተሜነት ሂደት ውስጥ በገቡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የከተሞችን ዘላቂ ዕድገትና ውበት ታሳቢ ያደረጉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ማከናወን ጥቅሙ ብዙ ነው።
የኢትዮጵያ ከተሞች የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና ከከተሞች መሪ ዕቅድ አኳያ በምን መልኩ አየተተገበረ ነው ሲል ኢዜአ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አመራር፣ ፋይናንስና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገመቹ እንደገለጹት፤ ለከተሞች ዘላቂ ዕድገትና ውበት ሲባል ከከተሞች ጠቅላላ ስፋት 30 በመቶው ለአረንጓዴ ልማት ስራ መዋል እንዳለበት በሕግ ተደንግጓል።
ሚኒስቴሩ በከተሞች የችግኝ አተካከል ሂደት፣ ቦታ መረጣን ጨምሮ ዝርዝር መስፈርቶችን የያዘ መመሪያ በማዘጋጀት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከከተማ ልማት ጋር አስተሳስሮ ለማስኬድ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በዚህም በፓርክ፣ የስፖርት ማዞተሪያ ሜዳዎች፣ የመንገድ አካፋይ፣ አደባባዮች፣የወንዝ ዳርቻዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ዘላቂ ማረፊያና በሌሎች ቦታዎች የችግኝ አተካከል መስፈርት እንደተቀመጠ ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ልማት ለነዋሪዎች፣ ለቱሪስቶችና ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ተወዳዳሪ ከተማ ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ክልሎችም በዚሁ አግባብ በየከተሞቻቸው መመሪያውን መተግበር እንደጀመሩ አንስተዋል።
በእስካሁን ሂደቶችም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደመጡ ጠቁመዋል።
በቀጣይም የሚካሄዱ የአረንጓዴ ልማት የከተሞችን ዘላቂ ዕድገትና መሪ ዕቅድ ባገናዘበ መልኩ የመትከል ስራን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ መዲና የሆነችውና ከኒውዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ችግኝ ከሚተከልባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ቀዳሚዋ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።
የከተማዋ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ እንደሚሉት፤ በከተማዋ የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ዘላቂ ጥቅምን እና የከተማዋን ተወዳዳሪነት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትግበራም በዚህ አግባብ እንደሚመራ ገልጸው፤ ይህንን ለማሳካትም ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ መልካ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ልማት መስፈርትን የጠበቀች ከተማ ለመገንባት ባለፉት ዓመታት ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
በአሁናዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትግበራም በሀገር አቀፍ መስፈርቶች መሰረት እንዲተከል ማህበረሰብ አቀፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በአረንጓዴ ልማት ሞዴልነት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ በሚል ከመረጣቸው 15 ከተሞች መካከል ሐዋሳ፣ ባህርዳርና ቢሾፍቱ ይገኙበታል።