ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር እና የግንዛቤ መፍጠር ስራን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን ይገባል- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር እና የግንዛቤ መፍጠር ስራን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን ይገባል- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
ሶዶ፤ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፡- ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር እና የግንዛቤ መፍጠር ስራን በጋራ ማስኬድ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
በሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውር ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን በመቀነስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ኮሚሽኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ቅድሚያ መከላከልን መሰረት ያደረገ የፍልሰት መቀነስ ስራ፣ የሕጻናት መብት ጥበቃ፣ እና የሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ቁጥጥር በማጠናከር ተጠያቂነት ማስፈን እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል በማሳየነት ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ ከአገር ውስጥ ባለፈ የውጭ ፍልሰትን ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ስደት የተሻለ አማራጭ አለመሆኑን ለማሳየት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ለሚመለከታቸው አካላት እየተሰጠ መሆኑንም ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የጠቆሙት።
ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውር ዘርፈ ብዙ ቀውስ እንደሚያስከትል በመገንዘብ ድርጊቱን በመከላከል መግታት እንደሚገባ እና ለዚህም የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው፤ በተለይ ህገ-ወጥ የህፃናት ዝውውር መንስኤ ከሆኑ ችግሮች መሠረታዊ ፍላጐት አለመሟላት ዋነኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በየአካባቢው የሚገኙ የልማት አቅሞችን ወደ ተግባር በመለወጥ የዜጎች ህይወት መቀየርና የተጀመረውን የትምህርት ቤት ምገባ ስራ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ-ወጥ ዝውውሩ የሚስተዋለው በራሳቸው ጤናማ ውሳኔ መወሰን በማይችሉ ህፃናት ላይ በመሆኑ ጉዳቱን የከፋ እንደሚያደርገው ተናግረው፤ እልባት ለመስጠት ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።
አስከፊ ችግር እየሆነ የመጣው ህገ-ወጥ የህፃናት ዝውውርን መከላከልና መቀነስ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ የገለጹት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ናቸው።
የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ስራዎች በማካሄድና አቅጣጫ የሚጠቁሙ ምክረ ሃሳቦች በማቅረብ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው፤ በችግሩ ምክንያት በዞኑ ዘንድሮ የትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ሲገባቸው ያልተገኙ ህፃናት በብዛት እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ዋናው መንስኤ ጊዜያዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ የአቻ ግፊትና ህገ-ወጥ ደላሎች መበራከት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ችግሩን ለመከላከል ከመንግስታዊ መዋቅሮችና የጸጥታ ሀይሎች ጋር በተከናወነው ስራ ውጤት መገኘቱንና አብዘኞቹ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ከመስጠት ባለፈ ህገ-ወጥ ደላሎችን በመከታተል አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ የችግሩን አሳሳቢነትና ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች በተመለከተ በዘርፉ ምሁራን የተደረጉ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
የፌዴራል፣ የክልልና የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኮንፈረንሱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።