የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገልጿል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት በአየር ትራንስፖርቱ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ሰፊ የመሰረተ ልማት እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ብዙ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በኮቪድ ምክንያት ሰራተኞቻቸውን በመቀነሳቸውና ገበያው ላይ አዳዲስ የሰው ኃይል ባለማግኘታቸው እየተፈተኑ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ነባሮቹን ባለመቀነስና አዳዲስ ባለሙያዎችን በማፍራት በስኬቱ ቀጥሏል ነው ያሉት።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2035 የረጅም ጊዜ ዕቅዱ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት በኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ 1 ሺህ 100 ተማሪዎች በተለያዩ ሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ዕቅዱን በማስፋትም በቀጣይ ዓመት 1 ሺህ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ነው የጠቀሱት።
አየር መንገዱ ዘንድሮ ከ170 በላይ አውሮፕላን አብራሪዎችን አስመርቆ ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቅሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን ለማፍራት ዕቅድ መያዙንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ያስታወቁት።
ለዚህም ጥር ወር ላይ የተመረቀው የሀዋሳ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተቋማዊ ስኬቱ ጠንካራ የስራ ባህል ግንባታን ከሰራተኞች ጥቅም ጋር አስተሳስሮ እየተጓዘ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህም የ17 ሺህ ቋሚ ሰራተኞቹን ጥቅም የማስጠበቅ ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።
በዚህም ሰራተኞች በራሳቸው ወጪ መኖረያ ቤት እንዲሰሩ ሲያስተባብር መቆየቱን ለአብነት ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ዙር ለ5 ሺህ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት የሚሆኑ ባለ 20 ወለል ህንጻዎች ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።