ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2015 (ኢዜአ)፦ በ2015 በጀት ዓመት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ገቢው በ10 ወራቱ ለማግኘት ከታቀደው 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ መሆኑንም ገልጿል።

ከተገኘው አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥም ግብርና 78 ነጥብ 26 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ 11 ነጥብ 76 በመቶ፣ማዕድን 6 ነጥብ 41 በመቶ ሲሆን ቀሪው ከስጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እና ከሌሎች የተገኘ መሆኑን አመልክቷል።

የወጪ ንግዱን ለማሳደግ በውል እና የኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ምርት የግብይት መመሪያና የምርት ገበያ አሰራር ስርዓት መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረጉ ተጠቅሷል።

ኮንትሮባንድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቦሎቄ ምርቶች የድንበር ላይ ኮታ እንዲነሳ መደረጉም ተገልጿል።

የወጪ ንግድ ምርት አቅርቦትን በመጠን እና በጥምርታ ለማሳደግ የአሰራር ስርዓት የመዘርጋትና የጫት ምርት የመላኪያ ዋጋ እንዲሻሻል ከጅቡቲ መንግስት ጋር በመወያየት የድጋፍና ክትትል ስራዎች መከናወናቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም