ቀጥታ፡

የካፒታል ገበያ አስተማማኝና ዘላቂ ኢንቨስትመንት ጥበቃን መሠረት ባደረገ መልኩ ይተገበራል- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን 

አዲስ አበባ  ሰኔ 8/2015 (ኢዜአ)  በቀጣይ ዓመት የሚጀመረው የካፒታል ገበያ አስተማማኝና ዘላቂ ኢንቨስትመንት ጥበቃን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የ6ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ዓመታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የመድን፣ የማይክሮ ፋይናንስ፣ የባንክና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማት ተወካዮችና ዓለም አቀፍ የሒሳብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ዶክተር ብሩክ ታዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ  ኃብት በማሰባሰብና ተገቢውን አቅርቦትን በማሳለጥ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ሁነኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የካፒታል ገበያ ስኬታማነት የሚረጋገጠው ምቹና ሀገራዊ መሠረት ያለው የቁጥጥር ሥርዓትና የኢንቨስትመንት ጥበቃ ሲደረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሥልጣኑ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የካፒታል ገበያ ሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ አስተማማኝና ዘላቂ የኢንቨስትመንት ጥበቃን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመተግበር በሚያስችል አግባብ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለሥልጣኑ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅትና ጥበቃ እንደሚያከናውንም ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያ አካል በሆነው የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ አገልግሎት ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችለው የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት በሁለት ወራት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

ፈቃድ የሚሰጥባቸው የአገልግሎት ዓይነቶች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ዓመትም ኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ይኖራታል ብለዋል።

በአፍሪካ በዘርፉ ልምድ ያለው የናይሮቢ ሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጂኦፍሬይ ኦዱንዶ በበኩላችው፤ ኢትዮጵያ  የካፒታል ገበያ ዕድሎችን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓን አድንቀዋል።

በካፒታል ገበያ ሰፊ ዕድሎችና ተዋንያን እንደሚኖሩት ገልጸው፤ ለካፒታል ገበያ ውጤታማነት በትምህርት ዘርፍ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ  ሰለሞን ደስታ በበኩላችው፤ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ከሚከናወንባቸው መስኮች መካከል የፋይናንስ ዘርፉ  አንዱ ነው ብለዋል።

በዚህም የፋይናንስ ተደራሽነት፣ አካታችነት፣ ብዝኃ አገልግሎትን፣ ለውጭ ኩባንያ ክፍት የማድረግ፣ በፋይናንስ ደኅንነት የማረጋገጥ፣ ዲጂታል አገልግሎትን ጨምሮ መልከ-ብዙ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ተወዳዳሪ፣ ጤናማ እና አካታች የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ተገቢውን የቁጥጥር እና ድጋፍ ሥራ  እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚሁ ሥራ ውጤታማነት የዘርፉ ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራዎች እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

እስከ ነገ በሚቀጥለው በዚሁ ጉባዔ በቀጣናው የፋይናንስ ዘርፍ አቅም፣ ቀጣናዊ ትስስር፤ የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነት፣ በቀጣናው የፋይናንስ ዘርፍ ውጤቶች አፈጻጸም፣ ልምዶች፣ የዘርፉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም