የመድን ድርጅቶችን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ሀገራዊ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የመድን ድርጅቶችን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ሀገራዊ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው- ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ ሰኔ 8 /2015 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የመድን ድርጅቶችን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ሀገራዊ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው 6ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ዓመታዊ ጉባዔ ጎን ለጎን ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የመድን ተቋማትን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ሀገራዊ ተቋም ለማቋቋም ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አጠቃላይ አሰራሩን በተመለከተ ከዓለም ባንክ ጋር በመቀናጀት ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ሂደቱም ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ጥናቶች ተጠናቀው ተቆጣጣሪ ተቋሙ ከተቋቋመ በኋላም ዘርፉን እንደ ባንኮች ሁሉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በቀጣይ ይከናወናሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ባንኮች በኩል ጥሬ ገንዘብ ዕጥረት አጋጥሟል በሚል የሚናፈሰው መረጃ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ከአስተዳደር ችግር ጋር በተያያዘ ስሙን ባልጠቀሱት በአንድ ባንክ ላይ ችግሩ መከሰቱን ጠቁመው፤ ይህም የስራ አመራር ማስተካከያ የሚሻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በድህረ ጦርነት ወስጥ ያለች አገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የተሻለ አቅርቦት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ከፍት የማድረግ ውሳኔን ተከትሎ የኢትዮጵያ የፋይናስ ተቋማት አቅማቸውን መገንባት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ተቋማቱ ከወዲሁ በሰው ሀብት፣ በቴክኖሎጂና በካፒታል አቅማቸውን መገንባት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።