ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑክ በኬኒያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ

ናይሮቢ፣ ሰኔ 8 /2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት የተመራ ልዑካን ቡድን በኬንያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ።

በቆይታቸው ከኬንያው ብሄራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኢንስፔክተር ጀነራል እና የAFRIPOL ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ጀነራል ጃፌት ኩሜ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተመላክቷል።

በውይይታቸውም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተለይም በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ሽብርተኝትን፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም የአደገኛ ዕፅ እና ህገ-ወጥ የቀንድ ከብት ዝውውሮችን በጋራ ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡


 

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ የኬኒያ ብሄራዊ ፖሊስ አገልግሎት ምክትል ኢንስፔክተር ጀነራል እና የወንጀል ምርመራ ኃላፊ መሀመድ አል አሚን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህም በቢሮው ሥር የሚገኙትን የኢንቲግሬትድ ኮማንድ ሴንተር እና የፎረንሲክ ምርመራ ቢሮን የጎበኙ ሲሆን በቴክኖሎጂዎቹ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መስማማታቸው ተመላክቷል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በእ.ኤ.አ ታህሳስ 08 ቀን 2022 የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡበትን በናይሮቢ የሚገኘውን የህብረቱ ድርጅት ፅህፈት ቤታቸውን እና የፀረ ሽብር ልህቀት ማዕከል መጎብኘታቸው ተገልጿል።

በጉብኝታቸውም በፅህፈት ቤቱ ከሚገኙ ሠራተኞች ጋር ተወያይተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ባጫ ደበሌም ተገኝተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ እና ሌሎች የተቋሙ አመራሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም