ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በተገቢው ክብር በማስተናገድ ረገድ አበረታች ሥራ እያከናወነች ነው-የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በተገቢው ክብር በማስተናገድ ረገድ አበረታች ሥራ እያከናወነች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኤጀንሲ አስታወቀ።

በታኅሳስ ወር 2016 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ፎረም ዝግጅት ላይ ያተኮረ አውደ-ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

አውደ-ጥናቱ በኢፌዴሪ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት እና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር.) ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር.) ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ፐንቨር አሊ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በገባችው ቃል-ኪዳን መሠረት ስደተኞችን ተቀብላ በተገቢው ክብር እያስተናገደች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ስደተኞች ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚያስችላቸውን አዋጅ በማጽደቅ ሥራና አገልግሎት የሚያገኙበትን መብት በማጎናጸፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገች መሆኗንም ነው ያብራሩት፡፡

በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር.) በኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ማማዱ ዲያን በበኩላቸው፤ ከጎረቤት አገራት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ 1 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ስደተኞች የትምህርት፣ ሥራና የኑሮ ሁኔታቸውን ለማሻሻል ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች የሕግ ማዕቀፍ ከመውጣቱ በፊት ስደተኞችን በአግባቡ የማስተናገድ ቀደምት ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ተናግረዋል።


 

አሁን ላይ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ሸሽተው ለሚመጡ ስደተኞች ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት የእንግዳ ተቀባይነትና የተቸገሩ ዜጎችን የመርዳት ታሪኳን እያስቀጠለች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 የጄኔቫ ስዊዘርላንድ መድረክ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አገራት የአሠራር ማሻሻያ፤ የማያስተናግዱ ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያዝ ቃል-ኪዳን መውጣቱን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም በትምህርትና፣ በአካባቢ እና በሕግ ጥበቃ ስደተኞችን ለማስተናገድ ቃል-ኪዳን መግባቷን ጠቁመው፤ በዚህም ስደተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ 129 ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመው፤ በጀርመን መንግሥት ድጋፍ 12 ሺህ ስደተኞች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ተወካዮችና ሌሎች የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም