የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ኩራትነቱንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ኩራትነቱንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ ሰኔ 08/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ኩራትነቱንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው የአየር መንገዱን በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በመቋቋምና ተወዳዳሪነቱን በማሳደግ የ2035 ራዕዩን ለማሳካት መሰረት የሚጥል አመርቂ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የአቪየሽን ዘርፉ ፈተና ቢሆኑም፤ ቻይናን ጨምሮ በኮቪድ በራቸውን የዘጉ ሀገራት በረራ መፍቀዳቸው፣ የመንገደኞች ቁጥር መጨመሩና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም መቋጨቱ መልካም አጋጣሚ ነበር ብለዋል።
አብዛኛዎቹ አየር መንገዶች ዘንድሮ በኮቪድ የተቋረጡ የበረራ መስመሮችን መልሶ ማስጀመር ላይ ሲያተኩሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮፐን ሀገን፣ አትላንታ እና ካራቺን ጨምሮ ሰባት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን በመክፈት ከሌሎቹ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ መንገደኞችን እንዲሁም 723 ሺህ ቶን ጭነት አጓጉዞ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 11 አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመግዛቱ አጠቃላይ የመንገደኞች አውሮፕላን ቁጥር ከ140 መሻገሩን ጠቅሰው፤ ረጅም ዓመት ያገለገሉ ሁለት የመንገደኞች አውሮፕላንን በምህንድስና ወደ ጭነት አገልግሎት ቀይሮ የጭነት አውሮፕላኖችን 15 አድርሷል ነው ያሉት።
የደንበኞች አገልግሎት ውድድር እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ በዚህ ውድድር አሸንፎ ለመውጣት አብዛኛዎቹ አውሮፕላኖች ለመንገደኞች የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ ማመቻቸቱን ተናግረዋል።
በዚህም የ2022 ምርጥ የአፍሪካ አየርመንገድ ሽልማትን ጨምሮ በርካታ እውቅናዎችን መቀዳጀቱንም ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ የበረራ አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም በጎሬ መቱ፣ ነገሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ደብረ ማርቆስ እና ሚዛን አማን የአውሮፕላን ማረፊያዎች እየገነባ ሲሆን ከፊሎቹ በቀጣይ ዓመት ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰው ኃይልና በመሰረተ ልማት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ እየገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአፍሪካ ከመንግስታትና ከባለሀብቶች ጋር በመሆን አየር መንገዶችን በማቋቋም ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህም ለአብነት የቶጎው አስካይ አየር መንገድን በማቋቋም ስኬታማ ተቋም እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በሌሎች ሀገራትም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ ላለፉት 77 ዓመታት ውስጣዊ አቅሙን በማጎልበት በፈጣን ዕድገትና በትርፋማነት መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን በማሳደግ እና መዳረሻዎቹን በማስፋት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራትነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።