ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለተጀመሩት ስራዎች መሳካት ድርሻችንን እንወጣለን-የጋምቤላ ነዋሪዎች

ጋምቤላ  ሰኔ 8/ 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለተጀመሩት ስራዎች መሳካት ድርሻቸውን እንደሚወጡ የጋምቤላ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተካሄዱ ላሉት ስራዎች የሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ለተባባሪ አካላት በጋምቤላ ከተማ በአዘጋጀው ስልጠና ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የተጀመረው ተግባር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡማን ኡኞንጎ በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉት አለመግባባቶችና ግጭቶች በምክክር ኮሚሽኑ እልባት ያገኛሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ የተጀመሩት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑም ድጋፋቸውና ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሰላምን ከሰይጣን በስተቀር የሚጠላ ሰብዓዊ ፍጡር ስለሌለ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለተጀመሩት ስራዎች መሳካት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ጆብ ፓል ናቸው።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም ለሀገራዊ የምክክር ሄደቱ የበኩላቸውን ሚና ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በስልጠናው መሰረትም ወደ መጡበት ሲመለሱ በሀገራዊ የምክክር መድረኩ የሚወከሉ ተሳታፊዎችን በኮሚሽኑ ባወጣው መስፈርት መሰረት የመለየት ስራ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ እንዳሉት ኮሚሽኑ  አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም ኮሚሽኑ እያከናወኗቸው ላሉት ስራዎች መሳካት የእያንዳንዱ ማህበረሰብ  ድጋፍና ትብብር እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቱን ጠቁመው፣ አሁን ላይ ለተባባሪ አካላት አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት በወረዳዎች የተሳታፊ አካላት ልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።  

ኮሚሽኑ ላለፉት ሁለት ቀናት በጋምቤላ ከተማ ለተባባሪ አካላት ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የሲቪክ ማህበራት፣ እድሮች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የፓርቲ ተወካዮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም