አደጋን አስቀድሞ በመከላከል ለችግር የማይበገር ማህበረሰብና ልማት ለመገንባት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
አደጋን አስቀድሞ በመከላከል ለችግር የማይበገር ማህበረሰብና ልማት ለመገንባት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ
ድሬዳዋ ሰኔ 8 / 2015(ኢዜአ) ፡- በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሊደርሱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ በመከላከል ለችግር የማይበገር ማህበረሰብና ልማት ለመገንባት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ምንነትና መፍትሄዎች ላይ የተደረገ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት ፤ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያቶች ሊደርሱ የሚችሉ የአደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ የመከላከል እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው።
በተለይ የተደራጀ የአደጋ ዝግጁነት ሥርዓት የመፍጠር፤ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ውጤታማ የመቆጣጠር ፣ህይወትን የማዳንና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ የሚሆኑት በጥናት ላይ የተመሠረተ የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል በማዘጋጀት ይሆናል ብለዋል።
እንደ አቶ ሀርቢ ገለፃ፤ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ የአደጋ መንስኤዎች ፣ተጋላጭነትና ያሉ አቅሞችን ተንትኖ መያዝና ተቀናጅቶ መተግበር ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብና ዘላቂ ልማትን ለመገንባት ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በድሬዳዋ አራቱ የገጠር ወረዳዎች አስቀድሞ እየተተገበረ የሚገኘው የጥናት ፕሮፋይል አደጋን በመከላከል ረገድ አበረታች ለውጥ እያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለከተማዋ የተዘጋጀውን ጥናት በሁሉም ሴክተሮች በተጠያቂነት በመተግበር ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ በሚሆን ደረጃ ውጤት ለማምጣት እንረባረባለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው፤ የከተሞች መስፋፋትና ውስብስብ ባህሪያት ለዘላቂ ልማት ዕድሎችን የሚፈጥረውን ያህል ለአደጋ ተጋላጭነቶች መጨመር አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
በሀገር ደረጃ የሚገነቡ ሁሉን አቀፍ ግዙፍ ፕሮጀከቶች ሆኑ በየከተሞች የሚገነቡ ልማቶች ከዕቅድ ጀምሮ በአግባቡ ለመምራትና ለመከወን እየተካሄዱ የሚገኙ የአደጋ ስጋት ጥናቶች ወሳኝ ይሆናሉ ብለዋል።
የሚዘጋጁ የአደጋ ስጋት የጥናት ፕሮፋይሎች ስኬታማ የሚሆኑት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በባለቤትነት በማሳተፍ ፣ ሁሉንም መንግስታዊ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተቀናጀ መንገድ ተባብረው ሲተገብሩት መሆኑን አስገንዝበዋል ።
በከተማ ደረጃ የተዘጋጀውን የአደጋ ስጋት የጥናት ፕሮፋይል ለልማት ዕቅዶች ምንጭ በማድረግ እና በተቀናጀ መንገድ በተጠያቂነት በመተግበር ከተማችን ምቹ የመኖሪያና የስራ መዲና እናደርጋታለን ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ጣሂር ሮብሌ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት ፤ ኮሚሽኑ አሁን ላይ ወቅቱን የሚመጥን አደረጃጀት ፣ አሰራርና ተቋማዊ ለውጥ በማምጣት በከተማ እና በገጠር የማህበረሰብን ህይወት፤ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ሃብቶችን ከአደጋ አስቀድሞ ለመታደግ እየሰራ ይገኛል።
ስራዎች በተለይ በከተማ ቀበሌዎች በተሻለ መንገድ ለመፈፀም የተዘጋጀው ጥናት ወሳኝ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የከተሞችን የአደጋ ስጋት ምንነትና መፍትሄዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በማስጠናት ላይ ሲሆን ፤በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተካሄደው የድሬዳዋ የዘጠኙ የከተማ ቀበሌዎች የአደጋ ስጋት አመራር የፕሮፋይል ጥናት የመጀመሪያው ሆኖ ድሬዳዋ ላይ ውይይት እንደተካሄደበት ነው የተመለከተው።