ልብን ለመጠገን የተዘረጉ በጎ እጆች - ኢዜአ አማርኛ
ልብን ለመጠገን የተዘረጉ በጎ እጆች
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015 (ኢዜአ) ልብን ለመጠገን የተዘረጉ በጎ እጆች
ሚኪያስ ጥላሁን የ12 ዓመት ታዳጊ ሲሆን ከሶስት ዓመት እድሜው ጀምሮ የልብ ህመም ተጠቂ እንደነበር ይናገራል፡፡
ወላጆቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸው መሆናቸው ደግሞ አስፈላጊውን ህክምና በወቅቱ እንዳያገኝ አድርጎት ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል በተደረገለት የቀዶ ህክምና አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የ5ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ መሆኑን ይገልጻል።
እንደ ታዳጊ ሚኪያስ ሁሉ በርካታ ህጻናት ከማዕከሉ ህክምና ለማግኘት ወረፋ በመጠበቅ ላይ ሲሆኑ፤ በጎ ፈቃደኞች ለማዕከሉ የሚያደርጉት ድጋፍ ደግሞ የህጻናቱን ህይወት በመታደግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው፡፡
ታዳጊ ሚኪያስ እርሱን ለማዳን የተዘረጉ በጎ እጆች ለሌሎች መሰል ህጻናት እንዲደርሱም ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አቶ ያሬድ አርገታ እንዲሁ የአራት ዓመት ህጻን ልጁ በልብ ክፍተት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃየ መሆኑን ይናገራል።
ህጻን ልጁ ከዘጠኝ ወሩ ጀምሮ የልብ ክፍተት ችግር እንዳለበት ያወቀ ቢሆንም የቀዶ ህክምናውን ባጠረ ግዜ ባለማግኘቱ ህመሙ እየበረታበት ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
ማዕከሉ ያለበት የህክምና መርጃ ግብዓት እጥረት ህጻናቱ ህክምና ለማግኘት ወራትን ብሎም ዓመታትን በወረፋ እንዲያሳልፉ ማድረጉን ነው የሚናገረው።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ አቅሙ በቻለው መጠን ማዕከሉን በመደገፍ ወገናዊ አለኝታነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርቧል።
ነዋሪነቷ በሰሜን አሜሪካ የሆነው ጋዜጠኛ ህይወት ታደሰ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም 50 ሚሊዬን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ጋዜጠኛዋ''ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ'' በሚል ሃሳብ የዛሬውን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ማድረጓን ነው ጋዜጠኛዋን ወክሎ ንግግር ያደረገው ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘርይሁን የተናገረው።
የህክምና ግብዓቶቹ በቀላሉ የማይገኙና በርካታ ህጻናት የቀዶ ህክምና እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጿል።
የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሕሩይ አሊ በበኩላቸው ጋዜጠኛ ህይወት የልደት ቀኗን ምክንያት በማድረግ ድጋፉን ማሰባሰቧን አንስተዋል።
ድጋፉ ለዓመታት ህክምናውን ለማግኘት ለሚጠባበቁ ህጻናትና ቤተሰቦቻቸው እፎይታን የሚሰጥ ስለመሆኑም እንዲሁ።
ጋዜጠኛ ህይወት ያደረገችው ድጋፍ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ እንዴት ማዋል እንደሚቻል በተግባር ያሳየ በመሆኑ የሚያስመሰግንና የሚበረታታ ነውም ብለዋል።
ይህንን በጎ ስራ በሁሉም ዜጋ ሊዘወተርና ባህል ሊሆን እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል በጋዜጠኛ ህይወት ከተቋቋመውና ''ላይፍ ፎር አፍሪካ'' ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በዘላቂነት መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡