ቀጥታ፡

የአረጋውያንን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል- የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015 (ኢዜአ) የአረጋውያንን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ጥሪ አቀረበ።

ማኅበሩ "ዓለም አቀፍ የአረጋውያን የጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን" ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና "ኸልፕ ኤጅ ኢትዮጵያ" ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር አክብሯል፡፡

የማኅበሩ ምክትል የቦርድ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሉ በዚህ ወቅት፤ የአረጋውያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ አሠራሮች በተገቢው መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተደራጀ አግባብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወን እንሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት፡፡

የአረጋውያን የኑሮ ሁኔታን መደገፍ ላይም በትብብር መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ማኅበሩ የአረጋውያን ችግሮች እንዲቀረፉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግብ ገብረሃዋርያ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በአረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመከታተል ትኩረት እንዲያገኙ ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን ምክረ-ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋውያንና የቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ  ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው፤ መንግሥት የአረጋዊያንን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ክልሎች የአረጋውያን ማዕከላትን በመገንባት ጭምር ክብካቤና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ  ግዙፍ የአረጋውያን ማዕከል ለመገንባት ዲዛይን መጠናቀቁንም ተናግረዋል። 

አረጋውያን የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ  እንዲሆኑም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም