በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ኃላፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ኃላፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡- በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር አህመድ ሞሐመድ አል ቴራይፊ ጋር ውይይት አድርገዋል።
የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በተለይም በንግድ፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ለአምባሳደር አህመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የፓን አፍሪካ መርሕ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸውላቸዋል።
የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር አህመድ ሞሐመድ አል ቴራይፊ በበኩላቸው ” ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እና ወደ አፍሪካ የመግቢያ በር ናት” ብለዋል።
ሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትስስራቸውን እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በቅርበት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሶስቱ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሏቸውን ልዩነቶች በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ይፈቱታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።