ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበጀት ዓመቱ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ተፅዕኖ እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የአቬሽን ዘርፍ ፈተና ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

ሆኖም አየር መንገዱ በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት ከ2035 የዕድገት ስትራቴጂ ጋር በማጣጣም ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አብራርተዋል፡፡ 

በተያዘው በጀት ዓመት በኮቪድ የተቋረጡ የበረራ መስመሮችን መልሶ ከማስጀመር በተጨማሪ ኮፐን ሀገን፣ አትላንታ፣ ካራቺን ጨምሮ ሰባት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን ጀምረናል ብለዋል።

በዚህም አየር መንገዱ ከኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከነበረበት የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የገለጹት። 

በበጀት ዓመቱ 11 አዳዲስ የመንገደኞች አውሮፕላን በመረከብ አጠቃላይ የመንገደኞች አውርፕላንን ከ140 በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ በሌላ በኩል ሁለት የመንገደኛ አውሮፕላኖችን በምህንድስና ወደ ጭነት በመቀየር የጭነት አውሮፕላኖችን ቁጥር 15 አድርሰናል ብለዋል፡፡ 

አየር መንገዱ በጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ መንገደኞችን እንዲሁም  723 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዙን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም አየር መንገዱ በጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን በማንሳት፤ ካለፈው ዓመት ሲነፃጻር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል። 

ገቢው የቀሪ ሁለት ሳምንታት አፈጻጸምን  ከግምት ውስጥ  ያስገባ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም