ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የሚወስዱትን የመውጫ ፈተና ለመስጠት በቂ ዝግጅት አድርገናል - ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የሚወስዱትን የመውጫ ፈተና መስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ፡፡  

በኢትዮጵያ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ ከሁሉም የመንግስት እና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ የትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን የሚያስመርቁ የግልና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናውን መስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟሉ መመሪያ መስጠቱም እንዲሁ፡፡

ኢዜአ የተቋማቱን ዝግጅት በሚመለከት የአዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎችን አነጋግሯል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እመቤት ሙሉጌታ እንዳሉት፤ የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የመማር ማስተማር ሂደቱን አቅጣጫ በማመላከት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ 

በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና በስኬት እንዲከናወን ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለተፈታኝ ተማሪዎች ማካካሻ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር በሞዴል ፈተናዎች ልምምድ እንዲያደርጉ እድሎች መመቻቸታቸውንም ነው የጠቀሱት፡፡ 

በዚህም ዪኒቨርሲቲው በ2015 ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሚያስመርቃቸው ሁለት ሺህ 993 ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ፤ ተቋሙ የሲቪል ሰርቪሱን አቅም በሚያጎለብቱ የትምህርት መስኮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

"ፐብሊክ ፋይናንሺያል ማኔጅመንት፣ ታክስ ኤንድ ከስተምስ አድሚኒስትሬሽን፣ አርባን ፕላኒንግ፣ አርባን ኢንጅነሪንግ" ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው የትምህርት መስኮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባባርም የመውጫ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ዪኒቨርሲቲው 223 ተመራቂዎች የመውጫ ፈተናው በስኬት እንዲወስዱ ለማድረግ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፈቀደ ቱሊ በበኩላቸው  ተማሪዎች ለመውጫ ፈተናው ከመቅረባቸው በፊት አቅማቸውን ማጎልበት የሚያስችል የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡


 

ዩኒቨርሲቲው የሚያስመርቃቸው 262 ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸው፤ ኦን ላይን ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና የሚሆኑ ግብዓቶች ተሟልተዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ እንደሚያግዝም ነው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ የተናገሩት፡፡ 

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፈቀደ ቱሊ፤ የመውጫ ፈተናው ዩኒቨርሲቲው ጥናትን መሰረት በማድረግ ለሚያሻሽላቸው ስራዎች ግብዓት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እመቤት ሙሉጌታ በበኩላቸው የመውጫ ፈተናው ውጤት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራቸውን መለስ ብለው እንዲቃኙ እድል የሚፈጥር ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም