ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ይሆናል-የብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት የሚሆንበት የምዝገባ ስራ እንደሚካሄድ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ስር በፕሮጀክት ደረጃ ሲሰራ ቆይቷል።

ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ስር ተዋቅሮ እየሰራ ሲሆን፤ አሰራሩን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስቀጠልም የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዳይሬክተር ሔኖክ ጥላሁን ለኢዜአ እንዳሉት የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በሙከራ ደረጃ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የማካሄድ፣ የዲጂታል መሰረተልማትን የማሟላት፣ የባለድርሻ አካላትን የማቀናጀት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

እንደ አቶ ሔኖክ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል የመታወቂያ ስርዓት የባዮሜትሪክ መረጃን በመጠቀም ለሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች ማንነትን በማረጋገጥ እና በኤሌክትሮኒክ መልኩ ደንበኞቻቸውን ማወቅ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ነው።


 

ይህም ስርዓት “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርህ የሚተገበርና ግለሰቦችን በስነ-ህዝብ እና በባዮ ሜትሪክ ማረጋገጫዎች ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ምዝገባው ሲካሄድ የስነ-ሕዝብ መረጃዎች ስም፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ አሁናዊ የመኖሪያ አድራሻ፣ ዜግነት እንዲሁም የባዮ ሜትሪክ መለያ የሚባሉትን የጣት አሻራ፣ የዓይን ብሌንና የፊት ገፅታ መረጃዎች ብቻ እንደሚፈልግ ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ በመሰረታዊነት የተመዝጋቢውን ማንነት ለማረጋገጥ አገልግሎት የሚሰጥ መታወቂያ ሲሆን ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራሙ የሙከራ ጊዜን ጨምሮ መተግበር ከጀመረ ወዲህ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማካሄዱን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም እየሰፋ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ የቴክኖሎጂን አቅም የማሳደግ እና ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ሰዎች በመላ ሀገሪቱ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምዝገባ እንዲያደርጉ መታቀዱን ገልጸዋል።

ዲጂታል የመታወቂያ ስርዓቱ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ የሚጠቅም ሲሆን በኢትዮጵያ በህጋዊነት የሚኖር ማንኛውም ሰው የብሔራዊ መታወቂያ ስርዓቱ ምዝገባ አገልግሎትን የማግኘት መብት እንዳለው ጠቅሰዋል።

አንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚመዘገብ ጠቅሰው፤ ምዝገባው ተረጋግጦ ለግለሰቦች የዲጂታል መታወቂያውን ተደራሽ ለማድረግ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደሚወስድ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት መታወቂያውን በካርድ ለሚፈልጉ ተመዝጋቢዎች ለመስጠት የህትመት ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ ሲሆን፤ መታወቂያውን የሚፈልጉ ማንኛውም ኢትዮጵያውያን ክፍያ ፈፅመው እንዲወስዱ ይደረጋል ብለዋል።

ለጊዜው የቴሌብር ሱፐር አፕ እና የብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ መተግበሪያ ስለተሳሰሩ ማንኛውም ተመዝጋቢ የቴሌብር መተግበሪያን በመጠቀም የዲጂታል መታወቂያውን ማግኘት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች ባለ 12 አሃዝ ልዩ የፋይዳ መለያ ቁጥር የሚሰጥ ሲሆን ይህም፤ የፋይዳ መታወቂያ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ እና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም