ቀጥታ፡

የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡-የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁ ።

ባለሀብቶቹ በአፍሪካ ያላቸውን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማስፋትም ኢትዮጵያን በዋና መዳረሻነት እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያበረታታ የኢንቨስትመንት ዕድል እና አማራጮችን የማስተዋወቂያ የበይነ መረብ ኮንፍረንስ ተካሂዷል፡፡

ኮንፍረንሱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጣሊያን ሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ሄሌኒክ አፍሪካ የንግድና የልማት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።


 

በጉባኤው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ለባለሀብቶቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በግሪክና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የሄሌኒክ አፍሪካ የንግድና የልማት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲቲሪስ ሞሶሪስ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።


 

የግሪክ ባለሀብቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው ፤ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ የንግድ ትስስር መዳረሻ የማድረግ አላማ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

በጉባኤው ከ30 በላይ የግሪክ ኩባንያዎች፣ የግሪክ ላኪ ማህበር አባላትና የአቴንስ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም በኢትዮጵያ የአውሮፓ የቢዝነስ ፎረም መሳተፋቸውን ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም