አምስት ሺህ 460 ግራም ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤቱ ይዞ የተገኘ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
አምስት ሺህ 460 ግራም ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤቱ ይዞ የተገኘ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ 5 ሺህ 460 ግራም ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤቱ ይዞ የተገኘ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 የደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ በሕገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድኑን በመኖሪያ ቤት በማስቀመጥ ለግል ጥቅሙ ሊያውል ሲል ፖሊስ ከሕብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መነሻነት በተደረገ ፍተሻ በመገኘቱ መሆኑን ገልጿል።
የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ የማዕድን ግብይት ውስጥ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ከማዕድን ዘርፋ የምታገኘውን ገቢ ለማሳጣት እየሰሩ ባሉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የጀመረውን ክትትልና ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
መንግስት የማዕድን ምርት በጠንካራ የግብይት ስርዓት ውስጥ አልፎ ለኢትዮጵያ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ሁሉም ዓይነት የማዕድን ግብይት እንዲስፋፋ እና ሕጋዊ ስርዓት እንዲይዝ በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
በመሆኑም ማዕድናትን በጥቁር ገበያ የሚገበያዩ እንዲሁም ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያከማቹ ግለሰቦች እና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለፀጥታ አካላት በመስጠት ሕብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።