ለኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ እና የምጣኔ ሀብት ሽግግር የመሬት እና ውሀ ሀብትን መጠበቅ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ነው - የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ እና የምጣኔ ሀብት ሽግግር የመሬት እና ውሀ ሀብትን መጠበቅ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ነው - የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡-ለኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳና የምጣኔ ሀብት ሽግግር የመሬት እና ውሀ ሀብትን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሀና መሬት ሀብት ማዕከል በውሃ እና መሬት ሀብት ጥበቃ እንዲሁም አጠቃቀም ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የጥናት እና ምርምር ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስና የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ለማምጣት እየተገበረቻቸው ያሉ መርሐ-ግብሮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል የ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ አንዱ መሆኑና ለመርሐ-ግብሩ ስኬታማነት የመሬት እና ውሃ ሀብት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በመተግበር እ.አ.አ በ2030 ንጹህ የመጠጥ ውሃን፣ ሳኒቴሽን እና የኃይል አቅርቦትን ሙሉ ለሙሉ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የምርምር ማዕከላት የውሃ እና መሬት ዘላቂ ምርታማነት በምርምር በመደገፍና የዘርፋን ተቋማት በአቅም ግንባታ በማገዝ ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለምጣኔ ሀብት እድገት ለፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለአገር ግንባታ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በጥናት እና ምርምር ጉባኤው ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ዲፕሎማቶች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣የልማት አጋሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በጉባኤው የውሃ እና አየር ንብረት ተጽዕኖ አስተዳደር፣ በአፈር ጥበቃ እና አስተዳደር፣ መሬት አስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።