ቀጥታ፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከካትሪን ሀምሊን የፌስቱላ ፋውንዴሽን የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡- የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከካትሪን ሀምሊን የፌስቱላ ፋውንዴሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ዶክተር ሊያ ውይይት ያደረጉት ከፋውንዴሽኑ የቦርድ ዳይሬክተር ጁሊ ዋይት፣ ከፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካሮሊን ሀርዲ እና ከፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ አስናቀ ጋር ነው።

የካትሪን ሀምሊን የፌስቱላ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የማህጸን ፌስቱላ ችግር ለተዳረጉ ሴቶች ሕክምና በመስጠት እና ፌስቱላ እንዲጠፋ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ሊያ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

የፌስቱላ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የሀምሊን ፌስቱላ ማዕከላት የሚያከናውኑት ስራ ለማጠናከር እና ፌስቱላን ለማጥፋት የተጀመረውን “ፕሮጀክት ዜሮ ኢኒሺዬቲቭ” እያደረገ ለሚገኘው የፋይናንስ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የካትሪን ሀምሊን የፌስቱላ ፋውንዴሽን የተቋቋመው በአውስትራሊያዊቷ ዶክተር ካትሪን ሀምሊን አማካኝነት እ.አ.አ በ1974 ነው።

ዶክተር ካትሪን በፋውንዴሽኑ አማካኝነት እንዲሁም በጽንስና ማህጸን ሙያቸው በፌስቱላ ችግር የሚሰቃዩ በርካታ ሴቶች ህክምና አግኝተው ጤናማ ኑሮ እንዲኖሩ አስችለዋል።

ለስድስት አስርት ዓመታት በሙያቸው ኢትዮጵያን ያገለገሉት ዶክተር ካትሪን ሀምሊን መጋቢት 2010 ዓ/ም በ96 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም