ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2015(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ ሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ እና ካናዳ ጠንካራ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አምባሳደር ምስጋኑ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከካናዳ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር በተለይም በፖለቲካ፣ንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር አሁንም በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፈን ጆቢን በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማጽናት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በማያያዝ አድናቆታቸውን እንደገለጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1965 ነው።
በየአገራቱ መሪዎች በቅርብ ጊዜያት የተደረጉ ጉብኝቶች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይነሳል።
እ.አ.አ በ2021 የወጣ መረጃ የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን 163 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ያሳያል።