አረንጓዴ አሻራ፤ የትውልድ ቅርስና ውርስ 

አረንጓዴ አሻራ፤ የትውልድ ቅርስና ውርስ 

(በይስሐቅ ቀለመወርቅ)

 እንደ መነሻ...

ዕጽዋት በሀመልማላዊነታቸው ለምድር ጌጥ ብቻ ሳይሆን ለጤናማ ሕይወት ዋስትና ናቸው። ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ ዘብ ናቸው። ዳሩ የሰው ልጅ ብዝኃ-ሕይወትን እያመናመነ፣ አካባቢውን እያዛባ፣ ምድርን እያጎሳቆለ... የዓለምን የምቹነት ዋስትና በራሱ እየተነጠቀ መምጣቱ እሙን ነው። በመሬት ላይ ቆይታው ቀጣይነት ያለው ጤናማ የሕይወት ዋስትና እንዳይኖረው በአንገቱ ላይ ሸምቀቆ አጥብቋል። 

ከሰዎች ዘፍጥረት እስከዛሬ ከትውልድ-ትውልድ የዕጽዋት መመናመን፣ የደን ሽፋን መራቆት፣ የአካባቢ መበከል.... ተዳምሮ የዓለምን ጉስቁልና እያባባሰው መጥቷል። ይህም የዓለምን ሕዝብ ለመልከ-ብዙ ቀውስ ዳርጓል። ይህን ሁሉን አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀልበስ በጊዜ መላ ካልተበጀለት ቀውሱ እየተባባሰ፣ የወደፊት ትውልድም ይበልጥ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ይቀጥላል። በተለይም የምግብ ዋስትና ችግር ላለበት ሦስተኛው ዓለም ሕብረተሰብ ችግሩ 'ከድጡ ወደ ማጡ' አድርጎታል። 

በዚህም ችግሩን ለመቀልበስ የአካባቢ ተቆርቋሪ ድምፆች በርክተዋል። የበረሃማነት መስፋፋትና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የተፈጥሮ ኃብትን መጠበቅና መልሶ ድነና አንዱ አማራጭ ነው። ለምድር ጤናማነት መመለስ ችግኝ ተከላ አንዱ ትኩረት ነው። 

በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1970 ጀምሮ የሚከበረው የዓለም 'የመሬት ቀን'ም ጤናማና ዘላቂ ከባቢ መገንባት፣ ለነገ ትውልድ የተሻለ ዓለም ማውረስን ለማበረታታት ያለመ ነው። የዓለም አርሶ አደሮች የአዝዕርት ዝርያዎችን ጠብቀውና አላምደው ዘመናትን ተሻግረዋል። ዳሩ በኢንዱስትሪና እርሻ መስፋፋት ሳቢያ 75 በመቶው የዕጽዋት ዝርያ መጥፋቱን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ  ያሳያል። "ሚሊኒየም ኢኮሲስተም አሰስመንት" የተሰኘ ድረ-ገፅ እንዳስነበበው ደግሞ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የዕፅዋት ዝርያዎች የሕልውና አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

በዚህም ባለድርሻ አካላት በየፊናቸው ችግኝ ተከላን በማስፋፋት የተፈጥሮ ሚዛንን ለመመለስ እየጎተጎቱ ነው። መንግሥታትም እንደየነባራዊ ሁኔታቸው የራሳቸው ተሞክሮ አላቸው። የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት፣ የምድር መጎሳቆልና የዕጽዋት መመናመን ጉዳይ ያሳሰባቸው ግለሰቦችና ተቋማት በየፊናቸው አመርቂ ተግባራት አከናውነዋል። ኢትዮጵያም በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ደን ድነና በዓለም ላይ ተጠቃሽ ተሞክሮ ሰንቃ ገብታለች።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ታሪክ  እና የደን ባለአሻራዎች ቅኝት

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ኃብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በሂደት ግን በብዝኃ-ሕይወት መመናመን ምክንያት ጥቅል የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ መውረዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረጉ ጥናቶች ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማደጉ ይነገራል።

የኢትዮጵያን የደን ልማት ጅማሮ መቼት በእርግጠኝነት ለመናገር አዳጋች እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘትና ቅርጹ ይለያይ እንጂ ነባር የችግኝ ተከላ ባህልና ልምድ እንዳለው ያወሳሉ። ያም ሆኖ በሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ ደን ድነናን መንግሥታዊ ቁርጠኝነት ወስደው የሰሩ መሪዎችም ነበሯት። ለአብነትም በመካከለኛው እና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ተሞክሮዎችን ማውሳት ይቻላል።

ከመካከለኛው ዘመን ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መካከል አፄ ዳዊት ከ1375- 1404 በነበሩ የግዛት ዘመናቸው ደን ጭፍጨፋና የእንስሳትን አደን ለመከላከል በአገሪቱ ሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች አቋቁመው እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይናገራል። ልጃቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብም በጅባት፣ በወፍ ዋሻ፣ የወጨጫን፣ መናገሻና የየረር ጋራዎችን የደን ክምችት ጥበቃ አጠናክረዋል፤ ‘የንጉሥ የደን ክልል’ አሰኝተው ኢትዮጵያን የደን ካባ ለማልበስ ጥረዋል።                                                      

ችግኞችን አፍልቶ የመትከል ሥራዎች ደግሞ በአፄ ልብነ-ድንግል ዘመነ-መንግሥት ስለመጀመራቸው ይወሳል። ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኘው የሱባ ደንም ንጉሠ-ነገሥቱ ከወፍ ዋሻ የዛፍ የሱባ/መናገሻ/ ደን ውስጥ ዛፎችን ስለመትከላቸው ይነገራል። በእርግጥ በመካከለኛው ዘመን ደን የመንከባከብና ዛፍ የመትከል ጅማሮ በዘመነ-መሳፍንት እንደተዳከመ ይነገራል።

ሌላው በደን ድነና ታሪካቸው የሚነሳው አፄ ምኒልክ ናቸው። የአፄ ዘርዓ ያዕቆብን ‘የንጉሥ ደን ጥብቅ ሥፍራ’ ጽንሰ-ሃሳብን አጠናክረዋል። በዘመናቸው ያጋጠማቸውን ፈተናም ለደን ድነና ተጨማሪ ኃይል የገፋፋቸው ይመስላል። አፄ ምኒልክ የደን የሕግ ማዕቀፍ አውጥተዋል፤ አማካሪም ቀጥረዋል። ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆንም ደንግገዋል። ፈጥኖ-አደግ የዛፍ ዝርያዎችን ከውጭ አስመጥተዋል። ዛሬ አገሪቷን የተቆጣጠረው አውስትራሊያዊው ባሕር ዛፍ (ኢካሊፕተስ) የትመጣነቱ ዳግማዊ ምኒልክ መሆኑ እሙን ነው። 

አፄ ምኒልክ በመንግሥት ከሚለማው ደን በተጨማሪ ተራው ዜጋ በባለቤትነት በደን ድነና እንዲሳተፍም አዋጅ አውጥተው እንደነበር የመዕዋለ ዜና ዘጋቢያቸው ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ጽፈዋል። አዋጁም ዛፍ የተከለ የመሬት ግብሩን ምሬዋለሁ የሚል ነበር። ለደን ጨፍጫፊዎችም ንብረታቸውን እንዲወረስና ብርቱ ቅጣት እንዲቀጡ ሕግ አርቅቀው እንደነበር ይወሳል። አፄ ምኒልክ ራሳቸው ከተከሏቸው ችግኞች መካከል በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን እና በደቡብ ወሎ ወረኢሉ ከተማ ይገኛሉ።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥትም ዛፍ መትከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደነበር ይነገራል። በደርግ ዘመን የተከሰተው ድርቅና ረሀብ ደግሞ በኢትዮጵያ ለሌላ ተጨማሪ የችግኝ ተከላ ዘመቻ መንስዔ ሆኗል። በደርግ ሥርዓተ-መንግሥት ችግኝ ተከላ እንደ አፄ ምኒልክ ለችግኝ ተካዩ ማበረታቻ የሚያሰጥ ተግባር ሆኖ እንደነበር ይነገራል። በአካባቢ ጥበቃ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች ተቀርጸው ገቢራዊ ተደርገዋል። በወቅቱ የተደረገው የተራቆቱ አካባቢዎችን በተለይም ተራሮችን ዛፍ የመትከል ዘመቻ ፍሬ አፍርቷል። ዛሬ በበርካታ የአገሪቷ አካባቢዎች የደን ጸጉር የለበሱ ተራሮች ሕያው ምስክር ሆነዋል። የደርግ ዘመን አረንጓዴ አሻራዎች ዛሬ የተራሮች አረንጓዴ ዕንቁ ሆነዋል። በደርግ ዘመነ-መንግሥትም የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከደን መመናመንና ከተፈጥሮ ኃብት መራቆት ጋር ተያይዞ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያጋጠማቸውን ቀውሶችና ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለምዕራቡ ዓለም አስረድተዋል፤ ተሟግተዋልም። አቶ መለስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እስከማለት ድረስ የዘለቁበትና ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቁት ፓኬጅም የሚጠቀስ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ቢኖሩም ዳሩ በዘመነ-ኢሕአዴግ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የደን ውድመት የደረሰበት ወቅት እንደነበር ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ኃብት መንከባከብን ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል። ከ2011 የክረምት ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ ‘አረንጓዴ አሻራ’ ገቢራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። በመላ አገሪቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ መርሃ-ግብሩ እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገ ተግባር ነው። አሁን ላይ ደግሞ የችግኝ መትከል ባህል ከመንግሥት ቅስቀሳና ከግለሰቦች ጥረት ባለፈ ሀገራዊ ቅርፅ የያዘ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቁ ማሳያ ነው።

በመሪዎች ደረጃ ይህን አነሳን እንጂ በየዘመኑ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማትም ተፈጥረዋል፡፡ ዛፍ እንደ ቅርስ፣ እንደ ሐውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ነውና በየዘመኑ ትጉ ሰዎች ለትውልድ ቅርስ ትተው አልፈዋል። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል አቶ ማሩ አበበ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ይገኙበታል።

በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጻፈው "የልማት አርበኛው ማሩ አበበ" የተሰኘው የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን የያዘው አጭር መድብል መጽሐፍ እንደሚያስረዳው በደቡብ ወሎ መቅደላ ወረዳ የተወለዱት አቶ ማሩ አበበ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ በትውልድ መንደራቸው ችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋም በደንና አካባቢ ልማት ሥራ በስፋት አካባቢያቸውን አልምተዋል። 

ለአብነትም የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር በደብረዘይት፣ ዶቃ ደብረሲና፣ በተንታ፣ በአንባ ማርያም፣ በለጋንቦና በሌሎችም የሀገሪቱ ልዩ ልዩ ቦታዎች መሰል የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል። ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም በአዲስ አበባ ቆይታቸው ኮተቤ ኪዳነምኅረትንና አሁን የእንጦጦ ፓርክ የተሰራበትን ሥፍራ ችግኞችን ማልማታቸውን ግለ-ታሪካቸው ያስረዳል። በደቡብ ወሎ ወረይመኑ ከፍተውት የነበረው የችግኝ ጣቢያም አሁን ድረስ ግልጋሎት እየሰጠ ነው። አቶ ማሩ አበበ በቅርቡ በደንና አካባቢ ልማት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ የሚዘክር ፕሮግራም በአዲስ አበባ ተደርጎ ነበር።

የአረንጓዴ አሻራ ክዋኔና ትሩፋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ2012ቱ የዓለም አካባቢ ቀን በተከበረበት ዕለት “ብዝኃ- ሕይወትን መጠበቅና መንከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና መሆኑን አይተናል” በማለት የአካባቢ ደኅንነት  የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ሌላው ክፍላተ-ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት ችግር ተጋርጦባታል፤ ለጎርፍ አደጋ፣ ለአፈር መሸርሸር፣ ለደን ጥፋትና ለብዝኃ-ሕይወት ኪሳራ ዳርገዋታልም ብለዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታዎችን የማመቻቸት አካል መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ግብ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊየን ዛፎችን ለመትከል ራዕይ እንድትሰንቅ እንዳስገደዳት ተናግረው ነበር።  ይህ አራት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ደግሞ ‘አረንጓዴ አሻራ’ ተሰኝቷል። በአረንጓዴ አሻራ ክዋኔም በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ተወጥኖ፤ አፈጻጸሙ ከዕቅድ በላይ 25 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸው ተገልጿል። የአራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ቀዳሚ ምዕራፍ ተጠናቆ፤ ዘንድሮ ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቅርቡ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

የአረንጓዴ አሻራ ቀዳሚ ምዕራፍ 

የመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ በ2011 ዓ.ም ክረምት ወቅት መባቻ ተጀምሮ ባለፈው ዓመት ነበር የተጠናቀቀው። በመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር መርሃ-ግብር በ2011 በይፋ ሲጀመር አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ በድምሩ 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ ነበር። ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ግቡን አልፎ በቀን 354 ሚሊየን ገዳማ ችግኞች ነበር የተተከሉት። በዚህ ዙር 20 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን አኑረዋል። 

በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2012 ዓ.ም 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል። በተለይ የፍራፍሬ ተክሎች ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።

ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሀሳብ ተተግብሯል። ይህም ዙር  ችግኞችን ለጎረቤት አገራት በመስጠት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ አርዓያ እንድትሆን በማስቻል ለየት ያለ ባህሪ ነበረው። ድንበር ዘለል ነበር። ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ችግኞችን መለገሷ ቅቡልነትን አስገኝቶላታል፤ ደንን በማልማት ጤናማ አካባቢ በመፍጠር ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖረንን ሰላም ለማረጋገጥም ያግዛል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተጀመረው ሦስተኛ ዙር መርሃ-ግብር  6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተከናውኗል።

አራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር  "አሻራችን ለትውልዳችን" በሚል መሪ ሀሳብ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ነበር። ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው በዚህ መርሃ-ግብር ከዕቅድ በላይ መሳካቱ ይታወሳል። 

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶክተር) በቅርቡ ባቀረቡት ሪፖርት በመጀመሪያው ምዕራፍ 25 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል። በየዓመቱ በአማካይ 20 ሚሊየን ሕዝብ ተሳትፏል። ከተተከሉት ችግኞች መካከል 52 በመቶ የጥምር ደን እርሻ፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ ናቸው። ሀገር በቀል ዝርያዎች ከፍተኛ ትኩረት ማግኘታቸውን አንሰተዋል። የፅድቀት መጠናቸው ደግሞ ከ80  በመቶ በላይ ተሻግሯል።

የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት ከ45 ሺህ ወደ 121 ሺህ ማደጋቸው፤ ከ700 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ነው። በአጠቃላይ በአራት ዓመቱ ትግበራ የማኅበረሰቡን ችግኝ ተከላና እንክብካቤ  ባህል አዳብሯል። መልከ-ብዙ  ማኅበራዊና  ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች አስገኝቷል።

የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት፣ ደረጃ፣ ጥራትና አቅም አድጓል። ከመጀመሪያው ምዕራፍ ትሩፋቶች መካከል አረንጓዴ የአኗኗር ዘይቤ መፈጠሩ፣ የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ በግማሽ እንዲቀንስ ማስቻሉ፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ለብዙዎች የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የተራቆቱ አካባቢዎችና ተፋሰሶች እንዲያገግሙ አስችሏል። ባገገሙ ተፋሰሶችም በርካታ አርሶና አርብቶ አደሮች በንብ ማነብና እንስሳት መኖ ልማት ዙሪያ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጧል። ለአብነትም የተተከሉ የአቮካዶ ችግኞች ለፍሬ መብቃታቸውን ተከትሎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በመደረጉ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ አምራች ለመሆን መብቃቷን ተናግረዋል።

'ነገን ዛሬ መትከል' ላይ ያተኮረው ሁለተኛ ምዕራፍ  

ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር መሪ ሀሳብ 'ነገን ዛሬ እንትከል' የሚል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በአፋር ክልል የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር ማስጀመራቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት እንዳሉት በቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ  25 ቢሊየን ችግኞች ይተከላሉ። እስከ ፊታችን መስከረም 2016 ዓ.ም በሚዘልቀው የዘንድሮው መርሃ- ግብርም 60 በመቶ የጥምር ደን እርሻ ችግኞች፣ 35 በመቶ ደግሞ የደን ችግኞች ሲሆኑ 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞች ናቸው። ለልጆቻችን ዕዳ ሳይሆን ልማትን ማሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል። በዚህም ዛሬ ያለው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተው ገልጸው ነበር።

'ነገን ዛሬ የመትከል ሥራችንን በአስተማማኝ ሁኔታ እያረጋገጥን በውጤታማነት ለመቀጠል እየሰራን ነው' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጥራት ጉዳይ የቀጣይ አረንጓዴ አሻራ ትኩረት እንደሚሆን ገልጸዋል። በተለይም ለፍራፍሬ እና ሀገር በቀል ዛፎች ቀዳሚ ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰዋል። እንደየመልክዓ-ምድሩ ዓይነት ተስማሚና በአጭር ጊዜ ለምግብነት የሚደርሱ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የራስ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያለመ ነው። ውበት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ገቢ አበርክቶ ያላቸው ችግኞች ላይ ይተኩሯል።

በቀጣይ አራት ዓመታት በአጠቃላይ 50 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን ገጽታ መለወጥ፣ በአፍሪካ  ቀዳሚ የአቮካዶ አምራች ሀገር  ማድረግ መሻት ያላት ሲሆን፤ ለስኬታማነቱም ጥራት ያለው ፖሊሲ ገቢራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል።  ያለ ልዩነት ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ስኬት መረባረብ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው ዓመት 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኞች ተዘጋጅተዋል፤ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችም ለተከላ ተዘጋጅተዋል። የተተከሉ ችግኞችን በቴክኖሎጂ መከታተል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ክትትል ይደረጋል። ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም የምግብ ዋስትናን እና የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ፣ የካርቦን ፋይናንስ ገቢን በሚያሳድግና የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ስኬትን በሚያግዝ መልኩ ይተገበራል።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የአገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው አየር ንብረትና መልክዓ-ምድር ለዚህ የሚጋብዝ ነው። ደን ልማት ዘላቂ ሥራ መሆን አለበት። ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ አሻራ መተግበር አለበት። የደን ልማት አካል የሆነው አረንጓዴ አሻራ አገራዊ ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። አገራዊ ፋይዳው ባለፈ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችን ተሸክሟል። የደን ልማት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው የሚሰኘውም ለዚህ ነው። ይህን ደግሞ ሰፊ ጉልበት ያለውን ሕብረተሰብ በዘመቻ መልክ አስተባብሮ ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቃል።

በመሪ ቃሉ እንደተመላከተው አረንጓዴ አሻራ የመጭው ትውልድ ቅርስና ውርስ ነውና፤ ሁሉም አሻራውን እንዲያሳርፍ ለተተኪው ቅርስ እንዲያወርስ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም