በሃገሪቱ በበጀት አመቱ 11 ወራት ከበጎ ፍቃደኞች 320 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ ውሏል - አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
በሃገሪቱ በበጀት አመቱ 11 ወራት ከበጎ ፍቃደኞች 320 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ ውሏል - አገልግሎቱ
አሶሳ ሰኔ 7 / 2015 (ኢዜአ)፡- በሃገሪቱ በበጀት አመቱ 11 ወራት ከበጎ ፍቃደኞች 320 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
20ኛው ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን "ደም ይለግሱ፤ ህይወትን ያጋሩ፤ ዘወትር ያጋሩ” በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በወቅቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች አስተዋጾ ባለፉት አስር ዓመታት ከነበረበት መሻሻል አሳይቷል፡፡
ለአብነትም በ2004 በጀት አመት ተሰብስቦ የነበረው 56 ሺህ ዩኒት ደም፤ በ2014 በጀት አመት ወደ 337 ሺህ ዪኒት ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት 427 ሺህ 320 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በ11 ወራት ውስጥ 320 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን አመልክተዋል።
የተሰበሰበው ደም ለጤና ተቋማት ተከፋፍሎ ለወላድ እናቶችና ቀዶ ጥገናን ጨምሮ ለተለያዩ ህክምናዎች እንዲሁም ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱባቸው አጋጣሚዎች መዋሉን አስረድተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ታዳጊ ሃገር ካላት ህዝብ አንድ በመቶ የሚሆነው በፈቃዱ ደም መለገስ እንዳለበት መስፈርት ማስቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ከሚጠበቀው 39 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፎ እየጨመረ ቢመጣም በቂ አለመሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም የመለገሰ ባህሉን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ ደግሞ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ተወካይ ዶክተር አሊባቦር ቡኖ በበኩላቸው "በሃገሪቱ የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ ፍትሃዊ የህክምና አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ ነው" ብለዋል ፡፡
"ይህ ጥረት የሚታገዘው ደግሞ በቂ የደም መጠን በጤና ተቋማት ሲገኝ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝ ጠቁመው በተለይም እናቶች በወሊድ ወቅት የሚከሰተውን ጉዳት በማስቀረት ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ማህበረሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንዳለበት ዶክተር አሊባቦር አስገንዝበዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለት የደም ባንኮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በደም ባንኮቹ ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበው ደም በክልሉ ከሚያስፈልገው 70 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ጠቁመዋል፡፡
እየተሻሻለ የመጣውን የክልሉን ሠላም በመጠቀም የደም ባንኮቹን አቅም በማጠናከር የደም ፍላጎት መጠንን ማሳደግ ቢሮው ትኩረት የሰጠው ጉዳይ መሆኑን ሀላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ላለፉት 10 ዓመታት ለ32 ጊዜ ደም የለገሰው የሀዋሳው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ሚፍታህ ተካ አንዱ ነው፡፡
"ደም በመለገሴ ከሞት ያዳንኳቸው ሰዎች ለእኔ እርካታዬ ናቸው" ያለው ወጣቱ በተከታታይ ደም በመለገሱ በጤናው ላይ የገጠመው እክል እንደሌለ ለኢዜአ አስረድቷል፡፡
በቀጣይ የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወጣቱ አመላክቷል፡፡
በበዓሉ ለረጅም ዓመታት ደም የለገሱ በጎ ፈቃደኞች በአገልግሎቱ እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ የጤና እና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲስተር አሚራ መሃመድን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ደም ባንክ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች በበአሉ ተሳትፈዋል፡፡