ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለአዲሱ ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ጋምቤላ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ)፡- ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለአዲሱ ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ኮሚሽኑ በጋምቤላ ከተማ ለተባባሪ አካላት ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል።


 

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ በሰላምና በእኩልነት መጪው ትውልድ ተከባብሮና ተፈቃቅዶ የሚኖርባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በአንድነት እንዲኖሩ ለማስቻል የምክክር መድረኩ በአግባቡ መተግበር እንዳለበት ጠቁመው፤ ለስኬታማነቱ ከተባባሪ አካላት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለአዲሱ ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ስራው ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የወጣቶች አደረጃጀትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ኮማንደር ጋድቤል ቦል በሰጡት አስተያየት፤ የምክክር መድረኩ ለሀገር ዘላቂ ሰላም የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ለሀገር ሰላም ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ከቀበሌ ጀምሮ ባሉት መዋቅሮች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ሌላው ተሳታፊ መምህር አማኑኤል በፍቃዱ ናቸው፡፡

ኮሚሽኑ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው ሥልጠና ላይ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተባባሪ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም