አፍሪካ እና እስያ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያስመዘግቡ የአህጉራቱ ወጣቶች ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ እና እስያ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያስመዘግቡ የአህጉራቱ ወጣቶች ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 7/2015 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ እና እስያ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ የአህጉራቱ ወጣቶች ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አመለከቱ።
በኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን አዘጋጅነት ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ እና እስያ ወጣቶች ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።
የፎረሙ ዓላማ የአፍሪካና እሲያን ወጣቶች በአንድ ላይ በማሰባሰብ በሰላም፣ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ ባህል፣ቱሪዝም፣በጎ ፈቃድ እና አየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ በጋራ በመወያየት እና ልምድ በመለዋወጥ ለዘላቂ ለውጥ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዲችሉ ማድረግ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አፍሪካና እስያ በልማት ዙሪያ የሚገጥማቸውን ችግሮች ለመሻገር ወጣቶች ማሳተፍ የግድ ይላቸዋል።
"እናንተ የአህጉራቱ ወጣቶች የነገ ብቻም ሳይሆን የዛሬ መሪዎች ናችሁ፤ "አህጉራቱ ውጤታማ የልማት ጉዞ እንዲራመዱ የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል" ብለዋል።
እንደ ዶክተር ኤርጎጌ ገለጻ፤ ወጣቶች ትልቅ አቅም በመሆናቸው የአህጉራቱ መሪዎች ወጣቶችን የሚያበቁ ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
የኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን የክብር አምባሳደር አክ ቦርሀሙዲን በበኩላቸው በርካታ አገራት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2030 ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ግብ እንደያዙ አንስተዋል።
ግቦቹ የሚሳኩት ወጣቶች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ቴክኖሎጂ፣ ጤና እና ሌሎች መስኮች ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው መሆኑን ገልጸው በዚህ ላይ አገራት የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመሆኑም የእስያ እና አፍሪካ ወጣቶች በጋራ የሚመክሩበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ መፈጠሩ ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል።
የአፍሪካ እስያ የወጣቶች ፎረም ተሳታፊ ወጣት ኬረን ዋኚ ዋኚ እንዳለችው አፍሪካና እስያ በኢኮኖሚ እና የራስን ገቢ በማመንጨት ረገድ እየተነቃቁ መሆኑን የሚታዩ ለውጦች አመላካች ናቸው።
እነዚህ ለውጦች ዘላቂ እንዳይሆኑ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት አህጉራቱ ሕዝብን ያሳተፈ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጻለች።
የ ኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን መስራች ከማል አብደላ በበኩላቸው ፎረሙ የአህጉራቱ ወጣቶች በስልጠና፣በስራ ዕድል ፈጠራ እና ልማት ላይ ሁሉን አቀፍ አበርክቶ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያም "በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደው የፎረሙ መድረክ የአህጉራቱን ወጣቶች ያቀረራበ እና ግቡን ያሳካ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
በአፍሪካ እና እስያ ወጣቶች ፎረም ከሁለቱ አህጉራት የተውጣጡ ወጣቶች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።