ቀጥታ፡

የጤና መድኅን አገልግሎት ከአባላት የተሰበሰቡ ገንዘቦችን ወደ ባንክ አስገብቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ከአባላት የሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ በማድረግ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። 

ቋሚ ኮሚቴው የጤና መድኅን ተደራሽነትና የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸም የ2013/14 በጀት ዓመት የዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።


 

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የጤና መድኅን ሥርዓትን ለማስፈጸም የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና አዋጆችን አውጥቶ በመተግበር በኩል ክፍተት እንዳለበት የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል።

በጤና መድኅን ዙሪያ ተከታታይነት ያለው የኅብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በበቂ ሁኔታ አለመሰጠቱና የጤና መድኅን አገልግሎት ለማግኘት የአባልነት መታወቂያ በወቅቱ ተዘጋጅቶ አለመሰጠቱንም ግኝቱ አሳይቷል። 

በተለይም በተለያዩ ክልሎች በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተቋማት ከአባላት የሚሰበስቡት ገንዘብ በወቅቱ ወደ ባንክ ገቢ ስለመደረጉ ክትትል እንደማይደረግ ተጠቅሷል። 

ያም ብቻ ሳይሆን የተሰበሰበውን ገቢ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ረገድ ክፍተት መኖሩም እንዲሁ። 

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ፤ ተሰብስቦ ወደ ባንክ ገቢ ያልተደረገውን ገንዘብ ክትትል በማድረግ ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ፤ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የኦዲት ማሻሻያ መርሃ-ግብሩን በአሥር ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴውና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት እንዲልክ አስገንዝበዋል።

ከአባላት ተሰብስበው ወደ ባንክ ገቢ ያልተደረጉ ገንዘቦችን በሦስት ወራት ውስጥ ገቢ በማድረግ ሪፖርት እንዲቀርብ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ከተደራሽነት፣ አገልግሎት ጥራትና የመድኃኒት አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችልና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር እንዲተገበርም አሳስበዋል።

በተጨማሪም የቅሬታ አፈታት ሥርዓትን መዘርጋት፣ የአባላትን መታወቂያ ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ማቀናጀት፣ ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በኦዲት ግኝቱ የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመጥቀስ የጤና መድኅን ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ከገቢ አሰባሰብ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ለዚህም የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን፣ የመረጃ አያያዝን በማዘመን፣ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም