የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አስተዳደራዊ በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠት አለባቸው - የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አስተዳደራዊ በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠት አለባቸው - የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ):- የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚሰጣቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች ገቢራዊ በማድረግ አስተዳደራዊ በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 የተቋቋመ የዴሞክራሲ ተቋም ነው።
ይህንንም ተከትሎ በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን መርምሮ ለእርምት እርምጃ የመፍትሔ ሀሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት "በገለልተኝነት ስራውን እየሰራ ነው"።
ለአብነት በ2015 በጀት ዓመት 11 ወራት ከ3 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ አቤቱታዎች መቅረባቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም 70 በመቶ በምርመራ መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።
በመንግስት አስፈጻሚ አካላት የደረሱ አስተዳደራዊ በደሎችን መርምሮ ተፈጻሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም ከሚደርሱን ችግሮች ብዛት አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል።
ተቋሙ "የታችኛው ማህበረሰብ ድምጽ የመሆን" ኃላፊነት የተሰጠው ነው ያሉት ዶክተር እንዳለ ተጠያቂነትን ለማስፈን በአስፈጻሚ አካላት ላይ ግልጽ ቁጥጥር እንደሚያደርግም አንስተዋል።
በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤትና መፍትሔ የእርምት እርምጃዎች ላይ ተባባሪ የማይሆኑ የመንግስት ባለሥልጣናት ተጠያቂነት እንዳለባቸው በአዋጁ ተደንግጓል።
በዚህም አስፈጻሚ አካላት በዜጎች ላይ በሚያደርሱት አስተዳደራዊ በደል፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራር መሠረት እርምጃ የማስወሰድ ኃላፊነት እንዳለበት ነው ዋና ዕንባ ጠባቂው ያመለከቱት።
ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በምርመራ ያረጋገጠውን ግኝት መነሻ በማድረግ የሚያቀርበውን የመፍትሔ እርምጃዎችን የሚወስዱ አስፈጻሚ አካላት ቁጥር ውስን ናቸው ብለዋል።
"ዜጎች ላይ የደረሰውን አስተዳደራዊ በደል በተመለከተ የቀረበላቸውን የመፍትሔ ሀሳብ ተግባራዊ የማያደርጉ አስፈጻሚ አካላት አሁንም ችግር እየፈጠሩ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚሰጣቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች ገቢራዊ በማድረግ አስተዳደራዊ በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
"ተቋማቱ የእርምት እርምጃ የማይወስዱ ከሆነ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እናቀርባለን" ሲሉ ዶክተር እንዳለ አስገንዝበዋል።