ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲደግፍ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርባለች።
ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እህሎች ጉባኤ በእንግሊዝ ለንደን ተካሄዷል።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አቶ በየነ ገብረመስቀል በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን እና የመቋቋሚያ እቅድ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እየሰጠች ያለውን የፖሊሲ እና የተግባር ምላሾች አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ በ10 የልማት መሪ እቅድ ውስጥ ተካቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ እና አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ላይ ያተኮሩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ በየነ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ዙር ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ጠቅሰው በቅርቡ በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እያደረገች ያለቻቸውን አገራዊ ጥረቶች በገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት፣ቴክኖሎጂ እንዲሁም ቀውስን መከላከያ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሾች ድጋፍ እንዲያደርግ ምክትል ሚሲዮን መሪው ጥሪ አቅርበዋል።
በዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እህሎች ጉባኤ የጥራጥሬ እህል ላኪዎች፣ የምርቶቹ ተቀባይ አጋር ድርጅቶች እና የመንግስት ተወካዮች መገኘታቸውን በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።