የቱሪስት መዳረሻዎችንና ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመጠገን፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪስት መዳረሻዎችንና ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመጠገን፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችንና ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመጠገን፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ የቱሪዝም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የትውልድ አሻራ ያረፈባቸው፤ ትናንትን የሚዘክሩ፣ የዛሬን ጸጋና ለነገ ትውልድ ስንቅ የሆኑ በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ናት።
በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በርካታ ሃብቶችን በዓለም ቅርስነት ካስመዘገቡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች።
ለዓለም ጎብኚዎች መዳረሻ ከሆኑ ጥንታዊ ቅርሶች መካከል አንዳንዶቹ በዕድሜ ብዛት እና በተፈጥሯዊና በሰው ሰራሽ ችግሮች ለጉዳት ሲዳረጉ ይስተዋላል።
ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም በጸጋዎቿ ልክ የቱሪስት መዳረሻ ልማትና ማስታዋወቅ ላይ ውስንነት እንዳለ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገልጸዋል።
በታሪካዊ ሥፍራዎችና ቅርሶች አካባቢ በቱሪስት መዳረሻዎች እሴት የመጨመር እና የማስተዋወቅ ሥራዎች በሚኒስቴሩ ውስን አቅም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችንና ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የማልማትና የማስተዋወቅ ተግባራት ግን የክልሎችና የግሉን ዘርፍን ብርቱ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
በቱሪዝም ስትራቴጂው የግሉ ዘርፍ እና የክልሎች ተሳትፎ እንዲጎለብት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለቅርሶች ጥበቃ፣ ጥገና እና ዕድሳት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የግል እና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ቅርሶችን መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ነው።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሕይወት ኃይሉ፤ ባለሥልጣኑ በተለይም ለብሔራዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ለትውልድ የማሻገር ተልዕኮውን ለመወጣት እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።
በታሪካዊ ቅርሶች ብዛት እና በባለሥልጣኑ የኃብት ውስንነት ምክንያት በቅርስ ጥገና እና ዕድሳት ላይ በሚፈለገው ልክ መከወን አለመቻሉንም ጨምረው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችንና ቅርሶችን በመጠበቅ፣ በመጠገን፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በተለይም የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም አስታውቀዋል።