ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ስነ ሕዝብ ፈንድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድሎች ፈጠራ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ):-የተባበሩት መንግስታት ስነ ሕዝብ ፈንድ(UNPFA) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድሎች ፈጠራ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር) ከተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ ኮፊ ኩዋሜ ጋር በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ውይይት አካሄደዋል።

ኃላፊዎቹ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ላይ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ መሰረት ያደረጉ፣ በስራ እድል ፈጠራዎች ዙሪያ ተጠቃሚ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ወጣቶች በቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማበረታታት በጀማሪ የስራ ፈጠራዎች እና የቴክኖሎጂ ሀሳቦች በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ ተነስቷል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ዘላቂ ልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ለማስቀጠል ወጣቶች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት የስነ ሕዝብ ፈንድ በበኩሉ ወጣቶች በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረጉ የስራ እድሎችን መፍጠር እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በቀጣይም ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ በአጭር እና ረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ተለይተው እቅድ እንዲወጣና ወደ ትግበራ እንዲገባ ከስምምነት ላይ መደረሱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም