ቀጥታ፡

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት በመንግስት ከፍተኛ ጥረት ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል- የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች

 

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015 (ኢዜአ)፡- በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት በመንግስት ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም እና መገንባት የጥናት ውጤት ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የምክክር መድረኩ ዓላማ በጦርነት የደረሰውን ጉዳትና በመልሶ ማቋቋም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ያተኮረ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ የሰሜኑ ጦርነት በአገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸው፤ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ችግሩን መቋቋም እንደተቻለ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የመልሶ ግንባታ ሥራውን የተሳካ ለማድረግ የግሉን ዘርፍና የልማት አጋሮችን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ፣ የፋይናንስና የዋጋ ደኅንነትን ማስጠበቅ የብሔራዊ ባንክ ሁነኛ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራው በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በጦርነት ለተጎዱ ባንኮች 10 ቢሊየን ብር ፈሰስ በማድረግ 8 ሺህ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አንስተዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በጦርነት አካባቢ ለነበሩ የጤና ተቋማት የኤች.አይ.ቪ.፣ የወባ፣ የእናቶችና ህፃናትን ጨምሮ ሌሎችም መድኃኒቶች ተደራሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከክልሉ ጤና ቢሮና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የጤና እና የስነ-ምግብ አገልግሎት ተደራሽ መደረጉንም ተናግረዋል።

የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀር በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ እንዲመለሱ ጥረት ስለመደረጉም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የጤና ተቋማት ወደ ተሟላ አገልግሎት እንዲገቡ የእገዛና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ጦርነትና ግጭቶች በተለይም ሴቶችና ህፃናት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም መልሶ ለማቋቋም "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መርህ የተለያዩ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በጉዳትና መልሶ ማቋቋም ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት የተሳተፉ የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ቀጣይ ለምታካሂደው የመልሶ ግንባታ ሥራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የዳሰሳ ጥናት በሸፈናቸው ክልሎች በማኅበራዊ፣ በምርት፣ በመሠረተ-ልማት እና ባለብዙ ዘርፎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊዮን ዶላር ውድመት መድረሱ በጥናቱ ተረጋግጧል።

በመድረኩም ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመልሶ ማቋቋም ግንባታ ፕሮግራም የ20 ቢሊዮን ዶላር መርሃ-ግብር ይፋ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም