ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳካት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግና የልማት አጋሮችን ትብብር ለማጠናከር ቅድሚያ ይሰጣል - ዶክተር በለጠ ሞላ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳካት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግና የልማት አጋሮችን ትብብር ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትኩረት ያደረገው ዊንጉ አፍሪካ ግሩፕ በ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በአዲስ አበባ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ ያስገነባውን ዘመናዊ የዳታ ማዕከል ዛሬ አስመርቋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዜጎችን አኗኗርና ህይወት ለማሻሻል በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መሰረት የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ነው።

በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽግግርን ለማሳካት የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከልም በዘርፉ  ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
 

የግል ዘርፉ ተሳትፎና የልማት አጋሮች ትብብር መጠናከር በዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ገንቢ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።

መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ እሴት የሚጨምሩና የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉ እንደ ዊንጉ አፍሪካ ካሉ  የቴክኖሎጂ ማዕከላት ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
 

የዊንጉ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ አንቶኒ ቮስካሪደስ፤ ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ለማንኛውም የህዝብና የግል ተቋማት በተመጣጣኝ ዋጋና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ በመረጃ ቋትነት እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

ዊንጉ አፍሪካ ሁሉንም አይነት ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀም፤ በሶማሊላንድ፣ ጅቡቲና ታንዛኒያ አገልግሎት የሚሰጥ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘ  የመረጃ ቋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሰፊ የታዳሽ ኃይል መኖሩ፤ ምቹ የአየር ጸባይና ሥነ-ምህዳር የታደለች በመሆኗ በቀጣናው ተመራጭ የዳታ ቋት ማዕከል እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል፡፡

የዊንጉ አፍሪካ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር ኒኮላስ ሎጂ ዛሬ የተመረቀው የዳታ ማዕከል በደንበኞች ምርጫ የኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪ ኮም ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል ፈጣንና አስተማማኝ የመረጃ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
 

በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያው እና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን  የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥና ወጭ ቆጣቢ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እንደሆነም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለኃብቶችም የደህንነት ዋስትና ያለው አማራጭ የመረጃ ቋት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

በቀጣይ በሀገሪቱ ያለውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ተጨማሪ የዳታ ማዕከላትን ለማስፋፋት የገበያ አማራጮችን እያጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም